ከአፍሪካ ተነስተው ወደ አውሮፓ እየተጓዙ የነበሩ ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን የጫነች ጀልባ በባህር ላይ ለ25 ቀናት ያህል ያለ አቅጣጫ ስትዋዥቅ ከቆየች በኋላ ቢያንስ 1መቶ43 ስደተኞች መሞታቸውን ወይም የት እንዳሉ አለመታወቁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል።
ከጋምቢያ ባፉሎቶ የተነሳችው እና መዳረሻዋ የስፔን ግዛት ወደ ሆኑት የካናሪ ደሴቶች እያቀናች የነበረችው ይህች ጀልባ ሐምሌ 11 ቀን የነፍስ አድን ስራ ተደርጎባት የሟቾች አስከሬን እና 38 በህይወት የተረፉ ሰዎችን ብቻ ይዛ ኑዋዲቡ ወደብ መድረሷን ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ቃል አቀባይ ማት ሳልትማርሽ፥በህይወት ከተረፉት መካከል በጉዞው ወቅት መላው የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጡ እና በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል በማገገም ላይ የሚገኙ ሁለት ህጻናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የሟቾቹ ዜግነት ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸው ቢታወቅም በትክክል በምን ምክንያት እንደሞቱ ግን ዝርዝር መረጃ አልተጠቀሰም።
ሞሪታኒያ በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የካናሪ ደሴቶች ለመድረስ የሚነሱባት መነሻ ሀገር ብትሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓ ህብረት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የስደተኞች ቁጥጥር ዘመቻ በመጠናከሩ የሞሪታኒያ ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን በከፍተኛ ሁኔታ በማባረር ላይ ይገኛሉ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ የአውሮፓ ህብረት የሚደግፈው እና ፍርሃትን የፈጠረው የስደተኞች ቁጥጥር ዘመቻ፥ስደተኞች ከተለመደው የባህር ጠረፍ ርቀው ይበልጥ ረጅም እና ገዳይ የሆኑ አማራጭ የባህር መንገዶችን ለመጠቀም እንዲገደዱ በማድረግ ለአደጋው መበራከት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
እድላዊት ብርሃኑ
ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም
