የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ የሀገሪቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርስኪን ከኃላፊነታቸው አንስተዋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትር ሚካይሎ ፌዶሮቭ ከሥራ ከተሰናበቱ ጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን፣ የዚያኔው ውሳኔ በሀገሪቱ በሙሉ የጎዳና ላይ ተቃውሞዎችን ቀስቅሶ ነበር።
የፌዶሮቭ ከኃላፊነት መነሳት በእሳቸው እና በሲርስኪ መካከል ከተፈጠረ አለመግባባት ጋር የተያያዘ ነው ተብለው መጀመሪያ የተሰራጩት ወሬዎች ብዙም ሳይቆዩ እውነትነታቸው ተረጋግጧል።
ዕድሜያቸው 35 የሆኑት ፌዶሮቭ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በማነቃቃት፣ የጦር ኃይሉን በመለወጥ እና የሙስና ተጋድሎውን በመምራት ረገድ ከፍተኛ ምስጋና የተቸራቸው ናቸው። በአንጻሩ ዕድሜያቸው 60 የሆኑት ሲርስኪ በብዙ ዩክሬናውያን ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጦችን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ፣ የቆየው የሶቪየት ወታደራዊ አስተሳሰብ ተከታይ አዛዥ ተደርገው ይታያሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሲርስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት የስንብት መልእክት የሥራ አፈጻጸማቸውን ሲከላከሉ፦ «ከሁለት ዓመት በፊት አስቸጋሪ የመከላከል ዘመቻ ያካሂድ የነበረ ሠራዊት አሁን በማጥቃት ላይ ይገኛል» ብለዋል።
አክለውም፦ «ለተካቼ አሁንም መስመሩን ጠብቆ ከመቆየት ባለፈ ወደፊት እየገሰገሰ ያለ ሠራዊት አስረክባለሁ… ይህ ማጥቃት ይቀጥላል ብዬ በሙሉ እምነት ተስፋ አደርጋለሁ» ሲሉ ጽፈዋል።
በሲርስኪ ቦታ ዕድሜያቸው 43 የሆኑት፣ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸውና በውጊያ የተፈተኑት ጄነራል ሚካይሎ ድራፓቲ ተክተዋቸዋል።
ድራፓቲ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ፦ «በተሟላ ትኩረት፣ በኃላፊነት ስሜት እና ዛሬ ሀገራችንን እየጠበቁ ላሉት ሰዎች ክብር በመስጠት እሠራለሁ» ብለዋል።
ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም
ዘሌንስኪ ለቀናት ከተካሄዱ ተቃውሞዎች በኋላ የዩክሬንን ከፍተኛ የጦር አዛዥ ከሥራ አገዱ
