ኢራን በቻይና የተሰሩ እስከ 400 የሚደርሱ በትከሻ የሚተኮሱ የአየር መከላከያ ሚሳኤል ማስወንጨፊያዎችን የመጀመሪያ ዙር ጭነት ከሳምንታት በኋላ ትረከባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ለሮይተርስ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ የሆነው ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር በገባችበት ጦርነት መከላከያዋን መልሳ ለመገንባት በምትሞክርበት ወቅት ነው።
ከ60 እስከ 70 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ዋጋ ያለው ይህ ግዢ፤ ቴህራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ የአጭር ርቀት አየር መከላከያዋን ለማጠናከር እያደረገችው ካለችው ትልቁ እንቅስቃሴ አንዱ ነው።
ጦርነቱ ኢራን ወታደራዊ ጣቢያዎቿን እና ስትራቴጂካዊ መሰረተ ልማቶቿን ከረቀቁ የአየር ጥቃቶች የመጠበቅ አቅሟ ላይ ክፍተት እንዳለ አመልክቷል።
ውሉ በቻይና የተሰሩ QW-12 እና FN-16 ሚሳኤሎችን ጨምሮ ከ300 እስከ 400 የሚሆኑ በሰው የሚንቀሳቀሱ በትከሻ የሚተኮሱ የአየር መከላከያ ስርአቶችን መግዛትን የሚያካትት መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል።
ምንጮቹ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሲሆን፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀረበለት አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ‹‹ዘገባዎቹ ሙሉ በሙሉ መሰረተ ቢስ ናቸው፤ ቻይና ሰላምን ለማምጣትና ግጭቱን ለማስቆም የበኩሏን ሚና በቋሚነት እየተወጣች ነው›› ብሏል።
ኢራን ላለፉት ወራት አሜሪካ እና እስራኤል በሚሳኤል፣ በድሮን እና በአየር መከላከያ ፕሮግራሞቿ ላይ ጥቃት ካደረሱባት በኋላ ራሷን መልሳ ማስታጠቅ አስፈልጓታል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ እነዚህ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን መረከቧ የኢራንን የአጭር ርቀት መከላከያ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሰፋ ሲሆን፤ከቻይና ጋር ያላት ወታደራዊ ግንኙነት እየጠነከረ መምጣቱንም ያሳያል።
በተያዘው ዕቅድ መሰረት ጭነቱ መጀመሪያ ከምዕራብ ቻይና ኡሩምኪ ተነስቶ በፓኪስታን በኩል ወደ ኢራን እንደሚጓጓዝ ተገልጿል።
ሆኖም የፓኪስታን ጦር የህዝብ ግንኙነት ክፍል ‹‹ፓኪስታን ከቻይና ወደ ኢራን ለሚላክ የአየር መከላከያ መሳሪያ ዝውውር እጇ አለበት የሚለው ግምት ፈጠራና ውሸት ነው›› ሲል አስተባብሏል።
እስከዳር ግርማ
ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
