የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኒውዮርክ ከንቲባ ቢቃወሟቸውም ወደ ኒውዮርክ እንደሚያመሩ አረጋገጡ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኒውዮርክ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ ተደጋጋሚ የእስር ጥሪዎች ቢደረጉባቸውም፣ በሚቀጥለው መስከረም ወር በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ያቀዱትን ጉዞ እንደማይሰርዙ በይፋ አስታወቁ።
ከንቲባ ማምዳኒ “ወደ አሜሪካ ከመጣ ይታሰር” የሚል ጥሪ ያስተላለፉ ቢሆንም ፣ ኔታንያሁ ከፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ዋይት ሃውስ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ “እውነትን ለመናገር ወደ ኒውዮርክ እሄዳለሁ” በማለት የከንቲባውን ንግግር አጣጥለዋል።
ከንቲባ ማምዳኒ በበኩላቸው በጋዛ እና በሊባኖስ በተከናወኑ ወታደራዊ ዘመቻዎች ምክንያት ኔታንያሁ “የጦር ወንጀለኛ” ናቸው ሲሉ ከሰዋል ፤ የፌዴራል አካላትም እንዲያስሯቸው ጥሪ አቅርበዋል።
“ወደ ኒውዮርክ እሄዳለሁ” ያሉት ኔታንያሁ ፤ “በዚህ ጥላቻን በሚዘራ እና የኒውዮርክ ነዋሪዎችን እርስ በርሳቸው በሚያጋጭ የተመረጠ ባለስልጣን ፊት እውነቱን ለመናገር እሄዳለሁ ” ብለዋል፡፡
ኔታንያሁ ማምዳኒ ጥላቻን እየነዛ ነው ሲሉ ከሰዋል። ንግግራቸውንም አጥብቀው በማውገዝ ዜጎችን በአይሁድ ማህበረሰብ ላይ ለማነሳሳት ሆነ ብለው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
“እኛ ያለነው በ1930ዎቹ ዓመታት ውስጥ ነው እንዴ? ይህ ምንድን ነው? እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥላቻ እና ውሸት!” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ፣ በተለይም በሊባኖስ ላይ የምታደርሰውን ቀጣይነት ያለው የአየር ላይ ጥቃት በመተቸት “እጅግ ብዙ ሰዎች እየተገደሉ ነው” ብለዋል።
የኒውዮርክ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ ቢል ደ ብላዚዮም የእስራኤሉን መሪ ለማሰር የቀረበውን ጥሪ በመቀላቀል ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
“እውነትን ለመናገር ወደ ኒውዮርክ እሄዳለሁ” አሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ
