የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማት መቆጣጠሪያ ጉድጓድ ክዳኖች ስርቆት በመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ

ባለስልጣኑ በ2018 የበጀት ዓመት ብቻ በስርቆትና በጉዳት የተነሱ ከ500 በላይ የመቆጣጠሪያ ጉድጓድ ክዳኖች መልሰው እንዲተኩ መደረጉን ለኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል።

​የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን፣ የክዳኖቹ ስርቆትና ውድመት አሁንም ለህዝብ ደህንነት ስጋት መሆኑና በጥገና ስራዎች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ለጣቢያችን ተናግረዋል።

​የጽዳትና የፍሳሽ መስመር ሰራተኞች  ለመቆጣጠሪያነት የሚጠቀሙባቸው እነዚህ የጉድጓድ ክዳኖች፣ በብረት ስርቆት ምክንያት በየጊዜው በመሰበራቸው ክፍት ሆነው ለተሽከርካሪዎችና ለእግረኞች ከፍተኛ አደጋ መደቀናቸውንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

​አቶ እያሱ በክረምት ወቅት ፈጣን የጥገና ሥራ የሚያስፈልጋቸው መንገዶች ላይ ጊዜያዊ ጥገናዎችን በማድረግ የክረምቱን ጊዜ መሻገርና መደበኛ የጥገና ሥራዎች እስኪጀመሩ ድረስ መፍትሔ የመስጠት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮንክሪትን ያህል ግንባታ ተሰብሮ ብረት የሚወሰድበት ሁኔታ ከህብረተሰቡ የተሰወረ ሊሆን አይችልም ያሉት ኃላፊው፣ ለዘላቂ መፍትሄ ህብረተሰቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነት በመጠበቅና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

አክለውም በቀጣይ ለስርቆት የማያጋልጡ አማራጮችን ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሀናን ሸምሱ

ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *