የዓለም ጤና ድርጅት ለካላ-አዛር በሽታ አዲስ እና አጭር የሕክምና መመሪያ ይፋ አደረገ

 የዓለም ጤና ድርጅት ለካላ-አዛር በሽታ ሕክምና የሚሆኑ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ለአጭር ጊዜ የሚወሰዱና ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኙ አዳዲስ መመሪያዎችን ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።
 
አዲሱ መመሪያ ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ ረጅም ጊዜ የሚወስዱና ከፍተኛ ሕመም የሚያስከትሉ የመርፌ ሕክምናዎችን በአፍ በሚወሰዱ መድኃኒቶች በተደገፉና ለታካሚ ምቹ በሆኑ አማራጮች የሚተካ ነው።
 
ቀደም ሲል በ17 ቀናት ውስጥ ይሰጡ የነበሩ 34 መርፌዎች ወደ 14 መርፌዎች (በቀን አንድ) ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል ብሏል ድርጅቱ ።
 
ከሕክምና በኋላ በሚከሰት የቆዳ ሕመም ምክንያት ታካሚዎች በሆስፒታል የሚያሳልፉት ከ60 እስከ 90 ቀናት የነበረው ቆይታ ወደ 14 ቀናት ብቻ አጥሯል።
 
በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ በተካሄዱ ክሊኒካዊ ምርምሮች የሕክምናው ውጤታማነት ከ90 በመቶበላይ መሆኑ ተረጋግጧል።
 
ሆኖም በአዲሱ ሕክምና ውስጥ የተካተተው ሚልቴፎሲን (MF) የተባለው መድኃኒት በፅንስ እድገት ላይ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል፣ በመውለድ እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች መድኃኒቱን ከመውሰዳቸው በፊት ከእርግዝና ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ድርጅቱ አሳስቧል።
 
በአሸዋ ዝንብ ንክሻ የሚተላለፈው እና ካልታከመ ለሞት የሚዳርገው የካላ-አዛር በሽታ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ እስከ 90 ሺህ አዳዲስ ታካሚዎች የሚመዘገቡበት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 79 በመቶ የሚሆኑት በምስራቅ አፍሪካ ይገኛሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ የበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሀገራት ብሔራዊ የሕክምና ማዕቀፎቻቸውን በአዲሱ መመሪያ መሠረት ያሻሽላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
 
ሐምሌ 27 /2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *