ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር አዲስ ድርድር እንደሚጀምሩ ተናገሩ፤ ኢራን «አዲስ ውሸት» ብላዋለች

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ለማካሄድ ያቀዱትን «ከባድ» የተባለ ወታደራዊ ጥቃት ማገዳቸውን ተከትሎ፣ ከሀገሪቱ ጋር አዲስ ድርድር በዛሬው ዕለት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

ትራምፕ ጥቃቱ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ጥቃት ይሆን እንደነበር ገልጸው፣አሁንም ቢሆን በማንኛውም ሰዓት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ብለዋል።

ኢራን በበኩሏ ከዋሽንግተን ጋር ምንም ዓይነት የፊት ለፊት ድርድር ለማድረግ የታቀደ ነገር የለም ስትል አስተባብላለች።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ልዑካንን የመቀበልም ሆነ ወደ ዋሽንግተን ተደራዳሪ የመላክ እቅድ የለኝም ብሏል።

የኢራኑ ሜህር የዜና ወኪል በበኩሉ ቴህራን አሜሪካን ጥቃት እንድታቆም ጠይቃለች መባሉ «አዲስ ውሸት ነው» ሲል ዘግቧል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት በፕሬዚዳንታዊው አውሮፕላን «ኤር ፎርስ ዋን» ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ጥቃቱ ሲሰናዳ ኢራናውያን ተመልክተውት ስለነበር የጥቃቱን አቅም ያውቁት ነበር ብለዋል። አክለውም «እየተነጋገርናቸው ነው፤ ድርድሩም ነገ ከሰዓት ይጀምራል» ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ቀደም ሲል «ትሩዝ ሶሻል» በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች በመያዛቸው ኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወዳጆች ጥቃቱ እንዲዘገይ ጠይቀውኛል ብለዋል።

በተለይም የሳውዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር ጥቃቱ እንዳይፈጸም ግፊት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ትራምፕ ሲናገሩም «ሁሉንም አዘጋጅተን ለመጀመር ተዘጋጅተን ነበር፤ ጥቃቱ እንዲቆም የጠየቁት ግን በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በኑክሌር ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ ነው» ብለዋል።

ቢቢሲ በዘገባዉ እንዳስነበበው ኢራን በኦማን አዘጋጅነት በሆርሙዝ ደህንነት ላይ የሚደረገው ድርድር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቃለች ብሏል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕን መግለጫ ተከትሎ በዓለም አቀፍ ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በዛሬው ዕለት የ4 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከዓለም አቀፉ የድፍድፍ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት 20 በመቶ ያህሉ የሚያልፍ በመሆኑ፣ የካቲት ወር የጀመረው ግጭት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ መዋዠቅ ሲፈጥር ቆይቷል።

ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *