የፈረንሳዩ ካናል ፕሉስ (CANAL+) ግሩፕ እስከ 2031 ድረስ ለሚቆዩ አራት የውድድር ዘመናት የሚቆይ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) በስሩ የሚያከናውናቸውን የወንዶች ክለቦች ውድድሮችን በከፊል የሳሃራ አፍሪካ አገራት በብቸኝነት የማስተላለፍ መብት ማግኘቱ ነው የታወቀው።
በዚህም መሰረት ይህ የፈረንሳዩ ግዙፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ፣ ዩሮፓ ሊግ እና ኮንፈረንስ ሊግ ጨዋታዎችን በሙሉ በብቸኝነት ያስተላልፋል።
ካናል ፕሉስ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ይህ ስምምነት ከ2027 አጋማሽ እስከ 2031 የሚዘልቅ ሲሆን፣ ከ40 በላይ የከፊል ሳሃራ አፍሪካ ሀገራትን ያጠቃልላል።
የቋንቋ እና የጣቢያዎች ክፍፍልን በተመለከተ በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት፦ የቻምፒየንስ ሊግ፣ የዩሮፓ ሊግ እና የኮንፈረንስ ሊግ ሙሉ ጨዋታዎች በካናል ፕሉስ ስፖርት (CANAL+ Sport) በፈረንሳይኛ ቋንቋ በብቸኝነት ይተላለፋሉ።
በእንግሊዝኛ እና ፖርቹጋልኛ ተናጋሪ ሀገራት ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት (SuperSport) የውድድሮቹ ዋና አስተላላፊነቱን አስጠብቆ ይቀጥላል።
ይህንንም ተከትሎ ከጣቢያው ጋር ትስስር የሚፈጥሩ ደንበኞች የአውሮፓውያኑን የክሊያን ምባፔ፣ አርሊንግ ሀላንድ፣ ላሚን ያማልና የመሳሰሉትን እንዲሁም የቪክቶር ኦሲሜን እና አዴሞላ ሉክማንን ጨምሮ የበርካታ አፍሪካውያን እና የአውሮፓ ከዋክብትን ጨዋታዎች መከታተል ይችላሉ ማለት ነው።
ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም
