በኢትዮጵያ የሚወጡ ሕጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሻሻሉ ወይም የሚሻሩ በመሆናቸው የሕግ ዋስትና ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ ተባለ፡፡
የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው ዓመታዊ የምርምር ጥናት ላይ፣ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መሐመድ ዳውድ ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ላይ ያደረጉትን ጥናት አቅርበዋል።
ለአብነትም አንድ አዋጅ ወጥቶ ሳምንት ሳይሞላው የተሻሻለበት ሁኔታ መኖሩንና ይህም በሕግ ሥርዓቱ ላይ ያለውን እምነት እንደሚሸረሽር ተናግረዋል።
በጥናቱ ከተነሱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፣ የሕግ አወጣጥ ሂደቱ በፖለቲካዊ ተጽዕኖ ሥር መውደቁና በቂ የሆነ የሕዝብና የሲቪክ ማኅበራት ተሳትፎ እንደማይደረግበት ተመልክቷል።
ይህም ሕጎቹ ጥራት የሌላቸውና በትግበራ ወቅት ችግር የሚፈጥሩ እንዲሆኑ ምክንያት መሆኑን አቶ መሐመድ አስረድተዋል።
በመጨረሻም ተመራማሪው፤ የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ የተረጋጋ እንዲሆንና በዘፈቀደ የሚደረጉ ለውጦች እንዲቀንሱ አሳስበዋል።
በተለይም የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማበረታታትና የሀገሪቱን የሕግ ማዕቀፍ ተዓማኒነት ለመጨመር የሕግ አወጣጥ ሂደቱ በሳይንሳዊና ግልጽ በሆነ መንገድ መመራት እንዳለበት ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም
