በኢትዮጵያ 79 የሚሆኑ ቋንቋዎች እንዳሉ በጥናት ማረጋገጡን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተናገረ

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በዉል ስንት እንደሆኑ የማይታወቁ እና መረጃም ያልተደራጀላቸዉ መሆኑን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናት መጀመሩን ከዚህ ቀደም በፓርላማ ተገኝቶ ገልፆ ነበር።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ቋንቋዎች አሉ የሚለዉን መረጃ የማሰባሰብ ስራ ሲከዉን መቆየቱን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዩች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታሁን ገዛኸኝ ለኢትዩ ኤፌም ተናግረዋል።

አቶ ጌታሁን እንደሚገልፁት እየተካሄደ በነበረዉ ጥናት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰባ ዘጠኝ ቋንቋዎች እንደሚገኙ አረጋግጠናል ብለዋል ፤ ሆኖም ጥናቱ ለመጨረሻው ግምገማ ዝግጅት ላይ መሆኑን ነግረዉናል።

ባለሙያዉ በተለምዶ ኢትዮጵያ 81 ያህል ቋንቋ አላት ተብሎ እንደሚነገር በማንሳት ይህንን ለማጥራት
አንድ አመት ፈጅቷል የተባለዉ ይህ ጥናት በመላዉ ሀገሪቱ በመዘዋወር መረጃ በማሰባሰብ እንደተደረገ ገልፀዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያቃቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ ቋንቋዎች 76 እንደነበሩ በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዩች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታሁን ገዛኸኝ ገልፀዋል።

ሚኒሰቴር መስሪያ ቤቱ ባደረገዉ በዚህ ጥናት ሶስት ተጨማሪ ቋንቋዎች የተገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የጥናቱን ሂደት ሲያስረዱም በመላዉ ሀገሪቱ ክልሎች ቡድን በማደራጀት እስከ ወረዳ ድረስ የቋንቋ ተናጋሪዎቹን በማነጋገር የተሰበሰቡ መረጃዎቹ የተደራጁ መሆናቸዉ ገልፀዉ ፤ ዉይይት እንደተደረገበት ነግረዉናል።

ሆኖም በጥናቱ ዙሪያ መጨረሻ የግምገማ ላይ ቀሪ ስራዎች መኖራቸዉን ጠቁመዉ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ጌታሁን ጨምረዉ ገልፀዋል።

ሆኖም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ አንድ ዘርፍ ጉዳዩን ለማጥራት ጥናት አጥንቷል ያሉት አቶ ጌትነት ገዛኸኝ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማጥናት ፍላጎት ካላቸዉ ጥናት ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ለትምህርት፤ ለሚዲያ እና ለፅህፈት አገልግሎት የሚዉሉ 63 ቋንቋዎች ተለይተዋል የተባለም ሲሆን ከነዚህ 63 ቋንቋዎች ዉስጥ 30 ያህሉን ዲጂታላይዝድ ተደርገዋል ተብሏል።

ቋንቋ የመዋጥ እድል ያለዉ በመሆኑ በመጥፋት ስጋት ላይ ናቸዉ የተባሉ ቋንቋዎችን የትምህርት ቋንቋ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ባለሙያዉ ይናገራሉ።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የቋንቋዎቹን መረጃ የመሰነድ ስራዎች አሉኝ ብሏል።

ቁምነገር አየለ

ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *