ጃፓናዊው የጣፋጭ ምርት አዘጋጅ ማቴ በጥቅል የቸኮሌት ወረቀት መልክ የተሰራና 0.03 ሚሊሜትር ብቻ ስፋት ወይም ውፍረት ያለው ‹‹ኮርቴክያ›› የተሰኘ ለየት ያለ የቸኮሌት ጣፋጭ ለገበያ አቅርቧል።
በ2024 ስራ የጀመረው እና በቶኪዮ ጃፓን የሚገኘው ማቴ ቦቴጋ ዴል ቾኮላቶ በዓለም ቀጭኑን ቸኮሌት በማዘጋጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ እውቅናን አትርፏል።
በጣሊያንኛ «የዛፍ ቅርፊት» የሚል ትርጉም የተሰጠውና «ኮርቴክያ» የተሰኘው ይህ ታዋቂ የቸኮሌት አይነት፤ በ0.03 ሚሊሜትር ብቻ የሚዘጋጅ በመሆኑ የኢንጂነሪንግ ድንቅ ስራ ተደርጎ ተቆጥሯል።
በጣሊያን ሀገር ጥንታዊ የቸኮሌት አሰራር ዘይቤ የተነሳሳው ኮርቴክያ፤ከአካባቢው የመሳሪያ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለአንድ ዓመት ተኩል ገደማ ጥናትና ምርምር ከተደረገበት በኋላ በተሰራ ልዩ ማሽን የታሸና የተጠቀለለ ነው።
ምንም እንኳን ተመሳሳይ ማሽኖች በሌሎች የዓለም ክፍሎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ እንደ ኮርቴክያ ያለ እጅግ ቀጭን የቸኮሌት ሽፋን ማዘጋጀት የሚችል ማሽን ግን እስካሁን አልተገኘም።
የ«ማቴ» መስራች ማቴኦ ዋና አላማ፤በአፍ ውስጥ ሲገባ ወዲያውኑ የሚቀልጥና ቀደም ሲል ተደርሶበት የማይታወቅ አዲስ የቸኮሌት ጣዕም ተሞክሮን ለደንበኞች ማቅረብ እንደሆነ ተገልጿል።
ቸኮሌት በአፍ ውስጥ ሊቀልጥ ሲል የተለየ ጣዕም እንደሚሰጥ የሚታመን ሲሆን፣«ማቴ» በየምግቡ ላይ ይህንን ልዩ ስሜት ለማቅረብ አልሞ የተነሳ ነው፡፡
ይህንን 0.03 ሚሊሜትር ውፍረት ያለው የቸኮሌት ሽፋን የዛፍ ቅርፊት በመሰለ ቅርፅ በመጠቅለል በአፍ ላይ ሲያርፍ ወዲያውኑ የሚቀልጥና አዲስ የምግብ አቀራረብ ስሜትን የሚፈጥር ልዩ የጣፋጭ አይነት መፍጠር ተችሏል።
ኮርቴክያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ ተቀባይነትን ካገኘ በኋላ ብዙዎች ተመሳሳይ ምርት ለማዘጋጀት ቢሞክሩም፣ ቸኮሌቱን ለማዘጋጀት የሚያገለግለውማሽን በቶኪዮ በሚገኘው የማቴ ቦቴጋ ዴል ቾኮላቶ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ልዩ መሳሪያ በመሆኑ እስካሁን ተመሳሳይ ምርት ማዘጋጀት አልተቻለም።
ሀና ሰይፉ
ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም
