ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባ ለጎብኚዎች ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ማለፊያ ብቻ መሆኗ ቀርቶ፣ ራሷን የቻለች የቱሪዝም መዳረሻ እየሆነች መምጣቷ ተገለጸ።
የቱሪዝም ባለሙያው አቶ አስናቀ አበበ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል ቱሪስቶች አዲስ አበባን በአብዛኛው ወደ ሌሎች ስፍራዎች ለመሸጋገር ብቻ ይጠቀሙባት ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ከተማዋን ራሷን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
በከተማዋ የተገነቡ በርካታ የቱሪዝም ልማቶችና ቱሪስቶች ከአንድ ቀን በላይ ቆይተው ሊጎበኟቸው የሚችሉ አዳዲስ መስህቦች መፈጠራቸው አዲስ አበባ የራሷን የቱሪዝም መዳረሻ ሚና እንድትይዝ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አቶ አስናቀ አንስተዋል። ይህም ጎብኚዎች በከተማዋ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲያራዝሙና አዲስ አበባን እንደ ዋና መዳረሻ እንዲመለከቷት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
በተያያዘም ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱና በፖሊሲ እንዲደገፍ መደረጉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ድርሻ እያሳደገው መምጣቱን ባለሙያው ጠቁመዋል። እንደ አቶ አስናቀ ገለጻ፣ ቱሪዝም በአሁኑ ወቅት እንደ ቡና ሁሉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚዘውሩ ዋና ዋና ዘርፎች አንዱ እየሆነ መጥቷል።
ሆኖም ዘርፉ አሁን ካለበት በተሻለ ደረጃ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችል ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያው አስገንዝበዋል።
ሰላማዊት ዲታ
ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከመሸጋገሪያነት ወደ ዋና የቱሪስት መዳረሻነት እየተሸጋገረች መሆኑ ተገለጸ
