የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋኢ፤ በኢራንና በአሜሪካ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ የተጠቀሰው የ60 ቀናት የድርድር ጊዜ ከአሁን በኋላ ተገቢነት እንደሌለው ገለጹ።
ባጋኢ እንደገለጹት፤ በሰነዱ ውስጥ በቀጥታ የ60 ቀናት የጊዜ ገደብ የሚል ድንጋጌ የለም፡፡
የ60 ቀናቱ ጊዜ የታሰበው በሁለት ዋና ጉዳዮች በኢራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በማንሳት እና የኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ ድርድር ለማድረግ ነበር።
በድርድሩ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ቢቀር ጊዜው ሊራዘምም ይችል ነበር፤ነገር ግን ኢራን እንደምትለው አሜሪካ ሰነዱ ከተፈረመ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የተስማማችባቸውን ጉዳዮች በመጣሷ ድርድሩ አልተጀመረም።
በመሆኑም የ60 ቀናት ጊዜ ገደብ ማስላት ከእንግዲህ ትርጉም የለውም ብላለች።
በተጨማሪም የኢራን ባለሥልጣናት ዋሽንግተን ወደ ቀድሞው የጊዜያዊ ስምምነት ውሎች እንድትመለስ እና የተስማማችባቸውን ግዴታዎች እንድትፈጽም ጠይቀዋል።
ትዕግስት ግርማ
ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም
