ሰራተኞች ማህበራትን ማደራጀታቸው እንደ ተቃዉሞ እና ችግር ፈጣሪ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲል ኢሰማኮ ተናገረ

‎‎ሰራተኞችን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ እንጂ ችግር ፈጣሪ አልያም ተቃዋሚ አድርጎ መመልከት አይገባም ያለዉ ኮንፌዴሬሽኑ፥ሰራተኞች በመደራጀታቸዉ እና ጥያቄ በማንሳታቸዉ የማህበር መሪዎች እየታሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
‎
‎ከ3 መቶ በላይ ህጋዊ እዉቅና ያላቸዉ የሰራተኛ ማህበራት እንዲደራጁ ተደርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተናግሯል።
‎
‎ኮንፌዴሬሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት አመት 4መቶ 28 መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበራት መደራጀታቸውን አስታዉቋል።
‎
‎የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ( ኢሰማኮ) የማህበር መሪዎች ያለ አግባብ የቦታ ዝዉዉር እርምጃ እና ሰራተኞች በመደራጀታቸዉ እስር እየገጠማቸው እንደሚገኝ ተናግሯል።
‎
‎የኮንፌዴሬሽኑ ኘሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፥እስከ ሰኔ 30 ድረስ ባለዉ ጊዜ 4መቶ 28 የሰራተኞች ማህበራት መደራጀታቸዉን ገልፀዉ፤3መቶ 45ቱ ህጋዊ እዉቅና ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
‎
‎የሰራተኞች ማህበራት እና በድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በድርድር መፍትሄ እንዲያገኙ፤ መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉትን ደግሞ በፍርድ ቤት መፍትሔ እንዲገኝላቸዉ የህግ ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል።
‎
‎የማህበራት መደራጀትን እንደ ተቃዋሚ መመልከት አይገባም የሚሉት የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት፥ ሰራተኞች ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ አጋዥ እንጂ ችግር ፈጣሪ ሆነው መታየት የለባቸውም ብለዋል።
‎
‎የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወስን የሚያስችለው ቦርድ እንዲቋቋም ደንብ ቢዘጋጅም እስካሁን መፅደቅ አለመቻሉን ገልጿል።
‎
‎በወር 1 ሺህ እና 2 ሺህ ብር ተከፍሎት የሚሰራ ሰራተኛ እየኖረ ነዉ ወይ? የሚሉት የኮንፌዴሬሽኑ ኘሬዝዳንት አቶ ካሳሁን፥ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል መወሰኑ ግዴታ መሆኑን እና ይህን ለማድረግ ግን ችግሮች እንደበዙ ተናግረዋል።
‎
‎ቁምነገር አየለ
‎
‎ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *