የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ ተወልደ ገብረማርያም የህንድ አየር መንገድ አዲስ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን በታታ ግሩፕ ስር የሚተዳደረውን አየር መንገድ መምራት መጀመራቸው ተዘግቧል።
በዋና መ/ቤቱ ከተደረገ የመጀመሪያ ስብሰባ በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ ለአየር መንገዱ የደህንነት ስርዓት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
የአየር መንገዱ ስራዎች በፍጥነት እያደጉ ባለበት በዚህ ወቅት የደህንነት ባህልን ማጠናከር ቀዳሚ ስራቸው መሆኑን የገለጹት አዲሱ ስራ አስፈፃሚ፣ “ኤር ኢንዲያን እንደገና ታላቅ እናደርገዋለን” በሚል መሪ ቃል አየር መንገዱን ተአማኒነት ወደሚጠበቅበት ከፍታ ለማድረስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ሲል ካፒታል አስነብቧል።
አቶ ተወልደ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአነስተኛ አህጉራዊ ተሸካሚ ወደ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኦፕሬተር ያሳደጉበትን ልምድ በመጠቀም፣ አሁን ላይ አየር መንገዱ ካለው ሰፊ የዕድገት ሂደት ጋር የተጣጣመ ጠንካራ የኢንጂነሪንግ፣ የጥገና እና የሰራተኞች ስልጠና ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል ርብርብ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም
