የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ህብረተሰቡ ያለ ስጋት እንዲያከብር የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስና ድንገተኛ ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት፣ የኔትዎርክ ፍተሻና የጥገና ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታወቀ።
ተቋሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመቀናጀት ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ ለ24 ሰዓታት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የቴክኒክና የጥገና ቡድን ወደ ሥራ ማስገበቱን ገልጿል።
አገልግሎቱ በላከልን መግለጫ ዋና ዋና የቴክኒክና የጥገና ሥራዎች አከናውኛሁ ብሏል
የመስመር ፍተሻ፡ በነሐሴ ወር በመላ አገሪቱ 2 ሺህ 110 ኪ.ሜ የመካከለኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተፈትሾ፣ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ 10 ሺህ 308 ግኝቶች ሙሉ በሙሉ ተስተካክለዋል።
የትራንስፎርመር ጥገናና ማሻሻያ፡ ከ8 ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮች ተፈትሸው በ6 ሺህ 877ቱ ላይ የተለዩ ችግሮች የተስተካከሉ ሲሆን፤ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ የዘይት መሙላት ሥራ ተከናውኗል።
አቅም ማሳደግ፡ የበዓሉን ከፍተኛ የኃይል ጭነት ለመቋቋም 178 ትራንስፎርመሮች (88 በአዲስ አበባ እና 90 በክልል ከተሞች) አቅማቸው እንዲሻሻል ተደርጓል።
ለደንበኞች የቀረበ ጥሪና የአገልግሎት መረጃዎች
ተቋሙ በበዓሉ ወቅት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማመጣጠን ደንበኞች ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙና በተለይም የኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት (ከምሽቱ 4:00 እስከ ንጋቱ 11:00) የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርቧል።
ጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአዲስ ዓመት በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወኑን ገለጸ
