ሁቲዎች ስትራቴጂካዊ የሆኑትን የቀይ ባህር ደሴቶች ተቆጣጠሩ

ተንታኞች የነዳጅ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል

በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ እንደ አዲስ ሊያገረሽ ይችላል የሚሉ ስጋቶች በጨመሩበት ወቅት፣ በኢራን የሚደገፈውና በየመን የሚንቀሳቀሰው የሁቲ አማፂ ቡድን ቁልፍ የሆነውን የባህር ንግድ መስመር የመቆጣጠር አቅሙን የሚያጠናክሩ ሁለት ስትራቴጂካዊ የቀይ ባህር ደሴቶችን በእጁ አስገብቷል።

አማፂው ቡድን በባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ አቅራቢያ የሚገኙትን ታላቁ እና ታናሹ ሐኒሽ ተብለው የሚጠሩትን ደሴቶችን ተቆጣጥሯል።

የአማጺው አባላት እነዚህን ደሴቶች መቆጣጠራቸው፣ ቡድኑ በባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ የሚገኘውን የሞካ ወደብ እና የፔሪም ደሴትን ከተቆጣጠረ በኋላ በየመን የቀይ ባህር ዳርቻ ያከናወነው ፈጣን ግስጋሴ አካል ነው ተብሏል።

የሁቲዎችን የፈጣን ግስጋሴ ተከትሎ በሳውዲ አረቢያ የሚደገፈው የየመን መንግስት በአማፂያኑ የተወሰዱበትን ቦታዎች ለማስመለስ እንዲዋጋ አስገድዶታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሪያድ በኢራን የሚደገፉት ታጣቂዎች በኢራቅ በኩል በዋና የነዳጅ መስመሯ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ለመቋቋም እየጣረች ትገኛለች።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ትላንት እንዳስታወቀው፣ በዚህ ወር በሁቲዎች እና በመንግስት ኃይሎች መካከል ያለው ውጊያ ከተባባሰ ወዲህ በየመን ወደ 94 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ከ2 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ በባህር አቋርጠው ወደ ጅቡቲ መሸሻቸው ተዘግቧል። የሁቲዎች ግስጋሴ በባብ አል-መንደብ ወሽመጥ ማዶ በምትገኘው ጅቡቲ ውስጥ ከሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ በ32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ እንዲገኙ አስችሏቸዋል።

ውጥረቱ የመተላለፊያ መስመሮች እንዲዘጉ በማድረጉ የነዳጅ ዋጋ ከሚገመተውም በላይ እንዳያሻቅብ ስጋት ፈጥሯል ሲል ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የሁቲ አመራሮች በቀይ ባህር ሁሉንም የንግድ እንቅስቃሴ ለማገድ ሳይሆን፣ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ቁርኝት ያላቸውን መርከቦችን ብቻ ኢላማ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። ከዓለማችን ትልቋ የነዳጅ ላኪ ሳውዲ አረቢያ የሚመጣው አቅርቦት ከመካከለኛው ምስራቅ ለሚመጣው የነዳጅ ገቢ ጥገኛ ለሆነው እና በዚህ የንግድ መስተጓጎል በከፍተኛ ሁኔታ ለተጎዳው የአፍሪካ እና የእስያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን በመቀነስ ዓለምን ከከፋ የነዳጅ ቀውስ ሲጠብቁ የነበሩት የነዳጅ ክምችቶች አሁን በአብዛኛው አልቀዋል።

አዲስዓለም አበበ

መስከረም 5/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *