የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመንገድ ልማት እና አስተዳደር ዙሪያ ሳይንሳዊ ምርምሮችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ከመንገድ ልማት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የመሬት መንሸራተት እና ናዳ ያሉ ክስተቶች ዋና የዘርፉ ችግሮች መሆናቸዉ ተገልጿል።
የአስተዳደሩ የምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር ወርቁ አስራቴ በዚህ ዘርፍ የግንባታ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናር እና የጥራት ጉዳይ የሚታወቁ ችግሮች መሆናቸዉን አንስተዋል።
ሆኖም አካባቢያዊ ክስተቶች አሁን እየመጣ ያለ ትልቅ አጀንዳ ነዉ ሲሉ ነግረዉናል።
እነዚህን ችግሮች በምርምር እና ቴክኖሎጂ መፍታት ካልተቻለ ለዘርፉ አስቸጋሪ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
አስተዳደሩ በመንገድ ኘሮጀክቶች ዙሪያ በምርምር እና ቴክኖሎጂ በመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፆል።
ዳይሬክተሩ “በቁፋሮ ወቅት ለግንባታ ምቹ የማይሆን አፈር ካለ እሱን አፈር አንስቶ በሌላ በሚስማማ አፈር መተካት ቢያስፈልግም ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ማቴሪያል ማግኘት ሳይሆን የሚደፋበት ቦታ እንኳን ማግኘት ከባድ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ ምርምር በማድረግ የነበረውን የተፈጥሮ ሁኔታ ባለበት መልኩ መጠቀም እንዲቻል ጥናት ሰርተናል ሲሉም አክለዋል።
አቶ ወርቁ አስራቴ እንደሚገልጹት ለዚህ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችም በሙከራ ደረጃ እየተሰሩ ስለመሆናቸዉ ነግረዉናል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር 9ኛዉን የመንገድ ጥናት እና ስርፀት ኮንፈረንስ ባካሄደበት ወቅት እንደገለፀዉ በዘርፉ ላይ ፈተና እየሆኑ ያሉትን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እና የመንገድ መሸራተት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች አቅርቧል።
ተቀምጠዋል ከተባሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዉስጥ በሲሚንቶ ኮንክሪት በሚሠሩ መንገዶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ በጥናት ተመላክቷል ተብሏል ።
ቁምነገር አየለ
መስከረም 7/2019 ዓ.ም
