በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ጤና ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የተቀናጀ የህፃናት እድገት ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉን ያስገነባው «ኔክሰስ ፎር ኢምፖወርመንት ኤንድ ዴቨሎፕመንት» (N4ED) የተባለው ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ከሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በጋራ በመቀናጀት ነው እውን ያደረገው።
የማዕከሉ መመረቅ በከተማ አስተዳደሩ ትኩረት የተሰጠውን የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በምርቃቱ እና በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የቢሮ ሃላፊዎች፣ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊዎች፣ የቀዳማዊ ልጅነት እድገት ክትትል፣ የህፃናት መብት ደህንነት እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ ዳይሬክተሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የማዕከሉን መከፈት ተከትሎ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚተገበረው የተቀናጀ የህፃናት ልማት ፕሮግራም በይፋ ተጀምሯል።
ስለ N4ED የበጎ አድራጎት ድርጅት
N4ED በቀዳማዊ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እንዲሁም ሴቶችን በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል ድርጅት ነው። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በድሬዳዋ፣ በሐረር እና በመቀሌ ከተሞች የተለያዩ የልማትና የበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመተግበር ላይ ይገኛል።
መስከረም 8/2019 ዓ.ም
የተቀናጀ የህፃናት እድገት ማዕከል ተመረቀ
