ቡሩንዲ ከራሷ ዜጎች ውጭ ከዩናይትድ ስቴትስ የተባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ከተስማሙ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ሆናለች።
የቡሩንዲ ዉሳኔ የተሰማዉ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፖሊሲው ላይ መደበኛ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የ‹‹ሦስተኛ ሀገር›› ዲፖርቴሽን እንዲቀጥል እንደሚፈቅድ ባስታወቀ በሰዓታት ውስጥ ነው።
የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ናንሲ ኒኔት ሙቶኒ ‹‹ፕሬዝዳንቱ ቡሩንዲ የምትቀበለው የወንጀል ክስ የሌለባቸውንና ከሽብርተኝነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች ብቻ እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል›› ብለዋል።
ቃል አቀባይዋ ለተባረሩት ሰዎች መጠለያ ለማዘጋጀትና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለመርዳት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ይህም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ እንደሚጠይቅ አክለው ተናግረዋል።
ቃል አቀባይዋ፤ አገራቸዉ ምን ያህል ስደተኞችን ለመቀበል እንደተስማማች ወይም መቼ እንደሚደርሱ ባይገልጹም፤ ቡሩንዲ ‹‹ችግር የገጠማቸውን ሰዎች ከመቀበል አኳያ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት›› ብለዋል።
ይህ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር ያጠናክራል። ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ ቡሩንዲ ደግሞ ለሰላምና መልካም ግንኙነት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የኢሚግሬሽን ቁጥጥር እርምጃዎቹ አካል አድርጎ በሦስተኛ ሀገር የሚፈጸሙ ዲፖርቴሽኖችን አስፋፍቷል።
አስተዳደሩ ይህንን ፖሊሲ፤ የዲፖርቴሽን ሰለባ የሆኑ ሰዎች ትውልድ ሀገራቸዉ እነሱን ለመቀበል እምቢተኛ በሚሆኑበት ጊዜ አስፈላጊ እርምጃ ነው በማለት ተከላክሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ ግን፤ ስደተኞችን ወዳልመጡበት ሀገር መላክ ለሕይወት አስጊ የሆኑ አስከፊ መዘዞች ሊኖሩት ስለሚችል እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
እስከዳር ግርማ
መስከረም 20/2019 ዓ.ም
