በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ይሆናል ተብሏል
በአሁኑ ወቅት ስራው እየተሰራ የሚገኘው በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ስር ተዋቅሮ እየሰራ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ 1284/2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል።
ይህም ስርዓት “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርህ የሚተገበርና ግለሰቦችን በስነ-ህዝብ እና በባዮ ሜትሪክ ማረጋገጫዎች ለመለየት የሚያስችል ነው።
ምዝገባው ሲካሄድ የስነ-ሕዝብ መረጃዎች ስም፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ አሁናዊ የመኖሪያ አድራሻ፣ ዜግነት እንዲሁም የባዮ ሜትሪክ መለያ የሚባሉትን የጣት አሻራ፣ የዓይን ብሌንና የፊት ገፅታ መረጃዎች ብቻ ያስፈልጋል፡፡
እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አካሂዷል።
የቴሌብር ሱፐር አፕ እና የብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ መተግበሪያ ስለተሳሰሩ ማንኛውም ተመዝጋቢ የቴሌብር መተግበሪያን በመጠቀም የዲጂታል መታወቂያውን ማግኘት ይችላል።(ኢፕድ)
ሰኔ 09 ቀን 2015 ዓ.ም
