ከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ÷የከተማ አስተዳደሩ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ከክልሉ መንግስት እና ሕዝብ ጎን በመቆም “ሀገር አፍራሽ እና የዘራፊ ስብስብ” ሲል የጠራውን ኢሰብአዊ ድርጊት በፅኑ እቃወማለሁ ብሏል፡፡
ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም እንደ ወትሮው ሁሉ ደጀንነቱን ያረጋግጣል! የከተማውን ሰላም በማረጋገጥ የህገ-ወጦችን ተግባር በህግ ሥርአት ያስከብራል! ሲልም ገልጿል።
ክልሉ ከጦርነት ጉዳት ሳያገግም በስሙ ምለው በሚገዘቱ የጥፋት ኃይሎች ይህን አይነት አስከፊ ችግር ስላጋጠመው እያዘነ ፤ እንደ አስፈላጊነቱ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ረገድ ከክልሉ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ይህንን አጥፊ ቡድን ኢሰብአዊ ድርጊቶቹን እንደሚቃወምም አስታውቋል።
የዚህ የጥፋት ኃይል ከአማራ ክልል ቀጥሎ አዲስ አበባን የሽብር እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ በተለያየ መንገድ እየሞከረ እንደሚገኝም ተደርሶበታል ነው ያለው በመግለጫው።
እነዚህ አጥፊ ቡድኖች እራሳቸው በጠመቁት የፀብ አጀንዳ አዲስ አበባን እና የአዲስ አበባን ህዝብ የአላማቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ ከተማዋን ደግሞ የግጭት እና ብጥብጥ አውድ ለማድረግ በተግባር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
