በጎረቤት ሀገር ሱዳን የሚገኙ ኢትጵያዉያን ዜጎች በጦርነቱ መክንያት ለሞት፤ ለስቃይና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸዉን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታዉቀዋል፡፡
ህይዎት በካርቱም እጀግ አስከፊ ስለመሆኑም ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ ኢትዮጵያዉን ነግረዉናል፡፡
ስድስት ወሩን ያስቆጠረዉ የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች እልቂት፣ ከሱዳናዉያን አልፎ በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎችን ህይዎት ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት መዳረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያመላክታል፡፡
ከታቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ በካርቱም ይኖሩ የነበሩ አሁን ላይ ወደ ሀገራቸዉ የተመለሱና እንዲሁም እዚያዉ የሚገኙ ዜጎች በሱዳን ያለዉን አስከፊ ህይዎት ነግረዉናል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ሀገረ ሱዳን እየወደመች መሆኑን የሚናገሩት እነዚህ ዜጎች አሁን ላይ ደግሞ ርሃቡ አይሏል፤ ዝርፊያና ግድያዉ ተባብሷል ነዉ ያሉት፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ኢትዮጵያዉን ዜጎች መገደላቸዉንም ይናገራሉ፡፡
አሁን በካርቱም ያለዉ ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ በመድረሱ በዚያ የሚገኙ ኢትጵያዉያን ለመሸሽ እንኳን አዳጋች ሆኖባቸዋል ነዉ የተባለዉ፡፡
ከጦርነቱ አምልጠዉ ወደ ሀገራቸዉ የተመለሱትና ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ ዜጎች፣ ከካርቱም እስከ መተማ የነበረዉ ጉዞ እጅግ አስከፊ እንደነበር አንስተዉ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ በአስቸኳይ እንዲደርስ ጠይቀዋል፡፡
በራሳቸዉ ወጪ ወደ ሀገራቸዉ የሚመጡ ኢትዮጵያዉያን ምእራብ ጎንደር ዞን መተማ ከተማ ላይ እየተደረገላቸዉ ያለዉ አቀባበል በቂ እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡
እኛም ይህ ለምን ሆነ ስንል የአከባቢዉን አስተዳደር ጠይቀናል፡፡
የምእራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከሱዳን ለሚገቡ ዜጎች የሚደረገዉ አቀባበል በሁለት መልኩ ነዉ ብለዋል፡፡ ይህም በኢትጵያ መንግስትና በአለም አቀፍ ድርጅቶች፡፡
ከሱዳን የሚገቡ ኢትጵያዉያን ዜጎችን በአካባቢዉ የተቋቋመዉ ግብረ ሃይል በተቻለዉ አቅም እየረዳ መሆኑን የነገሩን አቶ ቢክስ ፤ይሁን እንጅ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዉ መሄጃ የሌላቸዉ ኢትዮጵያዉያን አሁንም ችግር ዉስጥ ናቸዉ ብለዉናል፡፡
በርካታ ሀገራት በሱዳን የሚገኙ ዜጎችን በተለያዩ አማራጮች እያወጡና ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ካርቱም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምን እገዛ አደረገ ስንል ኤምባሲዉን ለማናገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ምላሽ አላገኘንም፡፡
በሱዳን በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ መግለጹ የሚታወስ ነዉ፡፡
በአባቱ መረቀ
ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም
