በእርሻ መሬቶች ላይ የሚደረገዉ ግንባታዎች በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የአድአ ጤፍ የሚባል አይኖርም ተብሏል።
ይህ የተባለዉ ረቡዕ ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የህዝብ ውይይት ባደረገበት ወቅት ነዉ።
“ሀገራችን ከፍተኛ የእርሻ ፍላጎት አላት በለሌላ በኩል ደግሞ የከተማዉ ፍላጎት አለ በተይም የኢንዱስትሪ፣የትራንስፖርት እና የማዕድን ፍላጎት አለ እነዚህ ሁሉ መሬት በመፈለጋቸዉ የመሬት ሽሚያ አለ ይላሉ አቶ ትዕግስቱ ገብረመስቀል የግብርና ሚኒስቴር የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ዋና ስራአስፈፃሚ።
ይህንን ከፍተኛ የሆነ የመሬት ፍላጎት በዕቅድ መምራት አለብን የሚሉት ስራ አስፈፃሚው ካልሆነ ግን ከፍተኛ የሆነ ግጭት ይፈጥራል ይላሉ።
እነዚህን አጠቃሎ የሚይዝ የመሬት ልማት ፖሊሲ አስፈላጊነቱን አፅንኦት ተሰጥቶታል።
ከአዲስ አበባ አቅራቢያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስፋፋያ በተመለከተ የጋራ መኖሪያ ቤትች ግንባታ፣በሞጆ አካባቢም የኢንዱስትሪ ግንባታዎች በእርሻ መሬት ላይ የሚከናወኑ ናቸዉ ተብሏል።
ግብርና ሚኒስቴር እነዚህን ችግሮች በመመልከት የሚፈታበት መንገዶችን በማጥናት ፖሊሲዉ የሚፀድቅበትን መንገድ እየሰራ ቢሆንም ባለመፅደቁ አዎጁ ላይ ማካተት አልተቻለም ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸዉ መታረስ የማይገባቸው መሬቶች እየታረሱ ስለሆነ ለአርሶ አደሮች አማራጭ የህልውና መሰረት በመስጠት መሬቱ እንዲያገግም እድል ማግኘት እንዳለበትና አጠቃላይ ሁሉንም ተቋማት ያካተተ ፖሊሲ እስኪወጣ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የበረሃማነት አደጋ ስጋት ያጋጥማል ብለዋል።
በአቤል ደጀኔ
ጥር 03 ቀን 2016 ዓ.ም
