በቦሌ አራብሳ ኮንደሚኒየም በተባባሰው ስርቆትና ዝርፍያ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ገለፁ፡፡

በመዲናዋ የወንጀል ድርጊት አስጊ ከሆነባቸው አካባቢዎች አንዱ እየሆነ የመጣው በለሚኩራ ክፍለከተማ የሚገኘው የቦሌ አራብሳ ኮንደሚኒየም ነው፡፡

በዚህ ኮንደሚኒየም ኑራቸውን ያደረጉ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ወጥቶ ለመግባት መቸገራቸውን ጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የአከባቢው ነዋሪ በአሁን ሰዓት በኮንደሚኒየሙ መንቀሳቀስ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱንና በተለይም በምሽት በተሸከርካሪ የታገዘ ዘረፋ እንደሚፈፀም ይናገራሉ፡፡

ኮንደሚኒየሙ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳና በቂ የፀጥታ አካል ባለመኖሩ የተነሳ በተደራጀ መንገድ በቀንም ሆነ በማታ በከፍተኛ ሁኔታ ዘርፋና ውንብድና ወንጀል እየተፈፀመ መሆኑን እንዲሁ የአካባቢው ነዋሪዎች ያነሳሉ፡፡

ሌላ ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው በአካባቢው በቀን ጭምር የሞባይል ነጠቃ በስለት የታገዘ ዝርፍያ በባጃጅ እና ሞተር ይፈፀማል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአራብሳ ኮንደሚኒየም ያለው የተደራጀ የወንጀል ድርጊት በሌሎች የአዲስ አበባ አካባዎችም በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡
ይሁን እንጂ ፖሊስ አሁንም ድረስ በሚሰጣቸው የተለያዩ መግለጫዎቹ የወንጀል ድርጊቶች መቀነሳቸውን መስማት የተለመደ ነው፡፡

በቅረቡም የተለያዩ ክፍለከተማ ፖሊስ መመሪያዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ በጋራ ባካሄዱት የሁለት ዙር ኦፕሬሽን የፖሊስ አመራሮችን ጨምሮ ከ5 ሺህ 536 በላይ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

የህብረተሰቡን ቅሬታ በተመለከተ ከጣብያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በለሚኩራ ክፍለ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት አመራር በአካባቢው ከቁጥጥር የወጣ የወንጀል ድርጊት የለም ብለዋል፡፡

እንደማንኛውም አከባቢ ወንጀሎች ሊፈፀሙ ይችላሉ እንጂ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚያሰጋበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ሲሉ ጣብያችን ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከሰሞኑ ባካሄደው ኦፕሬሽን 26 ሽጉጦች፣ 73 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ፣ በወንጀል ተባባሪ በመሆን የተጠረጠሩ የሜትር ታክሲዎች፣ እንደሚገኙበት ጠቁሟል።

ከዛም ባለፈ ከፖሊስ ተቋምም በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተሳትፈው የተገኙትን አመራርና አበላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው እንደሚገኝ መግለጫው አክሎ ገልጿል።

በአቤል ደጀኔ
ጥር 03 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *