51 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ እየተጣራ ነው ተባለ::

የ51 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ እየተጣራ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ይህን ያለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን የስድስት ወራት አፈፃፀም ሰሞኑን ከገመገመ በኋላ ነው።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የትምህርት ማስረጃ የማጥራት ሥራው ከታሰበው በላይ ቁጥሩ የሰፋ እና ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ የሚገኝ ነው።

ለትምህርት ማስረጃ የማጥራት ሂደቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰብሳቢነት የሚሳተፍበትና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የትምህርትና ሥልጠና እና የትምህርት ሚኒስቴር የተካተቱበት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ዲግሪና ከዲግሪ በላይ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው የ51 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ተሰብስቦ እየተጣራ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ዶ/ር ኃይሌ አስታውቀው፤ ከዲግሪ በታች የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሠራተኞች ማስረጃ የማረጋገጡ ሥራ በቀጣይ የትግበራ አካል እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ሥራው በአምስት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ኮሚሽነር ዶ/ር መኩሪያ የፌዴራል ተቋማትን፣ የሚኒስትሮችና የተጠሪ ተቋማትን ማስረጃ ማጥራት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኮሚሽኑ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ሶፍት ዌር እየለማ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መኩሪያ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጥራትና አስተማማኝነቱን ማረጋገጡንም ጠቁመዋል።

በልዑል ወልዴ
የካቲት 09 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *