በ2016 በጀት ዓመት ከ2መቶሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዞ የነበር ቢሆንም ማሳካት እንዳልተቻለ በክልሉ የቴክኒክ እና ሙያ እንዲሁም ስራ ፈጠራ ቢሮ ፤የስራ ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በርሄ ጸጋዬ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ነግረዉናል፡፡
ባለፈዉ በጀት ዓመት ለ2መቶ3ሺህ2መቶ88 ዜጎች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፤ማሳካት የተቻለዉ ግን ለ1መቶ36 ሺህ 6መቶ50 ዜጎች ብቻ ነዉ ብለዋል፡፡
ለእነዚህ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት አቶ በርሄ፤ ወደ ስራ በገቡ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችም ስራቸዉን መጀመራቸዉን ገልጸዋል፡፡
11ሺህ5መቶ ሁለት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ መግባታቸዉን የሚያነሱት አቶ በርሄ ፤ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በመንገድ እና የአከባቢ ጽዳት ላይ የተሰማሩ መሆናቸዉንም አንስተዋል፡፡
በታሰበዉ ልክ የስራ ዕድል እንዳንፈጥር ብዙ ችግሮች አሉብን ያሉን ዳይሬክተሩ፤ የብድር አቅርቦት አንደኛዉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከተለያዩ የብድር ተቋማት ለስራ ማስኬጃ በሚል ወደ 3.3 ቢሊየን ብር ለመስጠት ታቅዶ የነበር ቢሆንም፤ብድሩ ተመላሽ ሲደረግ 4 ቢሊየን ብር መሆን አለበት በመባሉ ይህንን ለማድረግ ሳንችል ቀርተናል ብለዉናል፡፡
እስከዳር ግርማ
