የህጻናት አስም

አለርጂ ሰዉነታችን አዲስ ለሆነ ነገር የተጋነነ ምላሽ ሲሰጥ የሚከሰት ነዉ፡፡
ታዲያ ብዙ የሰዉነታችን ክፍሎች በአለርጂ ይጠቃሉ፡፡ ከእነዚህ መሃከል አይን፣ አፍንጫ፣ አንጀት፣ ቆዳ፣ ሳምባ እና ሌሎች ናቸዉ፡፡
አስም ስንል ታዲያ በሳምባ ላይ የሚያጋጥም አለርጂ ነዉ፡፡

ስለ ህጻናት አስም ዶክተር አወቀች በሪሁንን አነጋግረናል፡፡
ዶክተር አወቀች በቅዱስ ጳዉሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የህጻናት ህክምና ስፔሻሊስት እና የሳምባ እና ጽኑ ህሙማን ሰብ ስፔሻሊስት ናቸዉ፡፡

በምን ይከሰታል?

የመጀመሪያዉ ከዘር የሚወረስ ሊሆን ይችላል፡፡
እንደ አቧራ፣በአይን የማይታዩ ጥቃቅን ብናኞች፣ ጠንካራ ሽታ/ጥሩም ሆነ መጥፎ ሽታ/
የአበባ ብናኝ፣ የሲጋራ ሽታ፣ በግድግዳ ላይ የሚኖር እርጥበት ፈንገስ እንዲፈጠር በማድረግ ምክንያት ይሆናል፡፡
ሽንት ቤት አከባቢ እና ቱቦዎች ስር ያለ ሽታ ሌላዉ መነሻ ምክንያት ነዉ፡፡

ምልክቶቹስ?

የመቆጣት እና የአየር ቧንቧ መጥበብ አንዱ ነዉ፡፡
በዚህም ምክንያት ልጆች ደረቅ ሳል ይኖራቸዋል፡፡
ሳሉ በቅዝቃዜ ሰዓት የሚባባስ እና ሌሊት ላይ ደግሞ እፍን በማድረግ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል፡፡
ጠዋት ከእንቅልፍ ሲነቁም ሳሉ ሊኖር ይችላል፤ በተጨማሪ ሲስቁ፣ ሲጫወቱ የሚኖር ሳል ሌላዉ ምልክት ነዉ፡፡
ተለቅ ያሉ ልጆች ሲሆኑ ደግሞ ደረት የማፈን ስሜት እንዳላቸዉ ሊናገሩ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ ደረት ማፈን፣ አየር ለማስወጣት መቸገር፣ ሳል፣ ቶሎ ቶሎ መተንፈስ ናቸዉ፡፡

የአስም ህመም ከልጅነት የሚጀምር ቢሆንም ጨቅላ ህጻናት ላይ ግን አይስተዋልም፡፡

ከ3ወራት ጀምሮ ግን ሊከሰት ይችላል፡፡
ነገርግን ከ 6ወራት በላይ ያሉ ልጆች ሆነዉ ቆዳቸዉን የሚያሳክካቸዉ፣የአፍንጫ፣ የአይን አለርጂ ካለባቸዉ፣ሳሉ የሚሄድ የሚመጣ ከሆነ፣ ደረቅ ሳል ከሆነ እና በቅዝቃዜ ሰዓት የሚባባስ ከሆነ አስም የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነዉ፡፡

መፍትሄዉስ?

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ ምርመራ አድርጎ ህመሙ መከሰቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ህመሙ መታከም የሚችል መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር አወቀች ፤ ህመሙ ባይድንም ግን እንዳይነሳ ማድረግ ይችላል ይላሉ፡፡

ህክምናዉስ?

ሁለት ዓይነት ነዉ፡፡ ከባድ የሆነዉ እና ደረትን የሚያፍነዉ ደረጃ ላይ ከደረሰ ሆስፒታል መግባት እና የኦክሲጅን ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

አብዛኛዉ ግን እየሄደ እየመጣ የሚቆይ ሳል ከሆነ ወደ ሆስፒታል መሄድ ብዙም ስለማይታሰብ አብሯቸዉ እንዲያድግ እና ለሳምባ ህመም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡

የአስም ህመም ህክምና ሲሰጣቸዉም ሰዉነታቸዉ ቶሎ ምላሽ እንዳይሰጥ ያደርጋል፡፡
ስለዚህ ይህንን ምልክት የሚያስተዉሉ ወላጆች ሳይዘናጉ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ማሳከም ተገቢ ነዉ፡፡

እስከዳር ግርማ

ሐምሌ 5 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *