የአዉሮፓ ህብረት የዉጪ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል፤ሃንጋሪ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ባላት አቋም ምክንያት ቀጣዩ የዉጪ እና የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ አገሪቱ ላይ እንደማይካሄድ ገልጸዋል፡፡
ይህ ክስተት የተፈጠረዉ ሃንጋሪ በተለምዶ ዝግጅቱን የምታስተናግድበትን የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ተለዋጭ ፕሬዝዳንትነት ከተቀበለች ከሳምንታት በኋላ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሞስኮ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ነዉ፡፡
ቦሬል የሃንጋሪ እንቅስቃሴ መዘዞች አሉት ስለሆነም እኛ ምልክት መስጠት ነበረብን ያንንም ነዉ ያደረግነዉ ብለዋል፡፡
ሃንጋሪም ዉሳኔዉን ‹‹ፍጹም የልጅ ጨዋታ ››ነዉ ስትል ገልጻዋለች፡፡
በየስድስት ወሩ አዳዲስ ተለዋጭ ፕሬዝዳንቶችን በመምረጥ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮች ህብረቱን እያጋጠሙ ባሉ ትልልቅ አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ ያደርጋሉ።
ቀጣዩ ስብሰባ ከነሃሴ 28-30 ድረስ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበር ቢሆንም ፤ጆሴፍ ቦሬል ግን በብራሰልስ ይካሄዳል ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከ26ቱ የአዉሮፓ ህብረት አገራት መካከል በዚህ አለመግባባት ለሃንጋሪ ድጋፏን የሰጠች አገር ስሎቫኪያ ብቻ ናት ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም
