ሲንዋር ከዚህ ሹመት በፊት የሐማስ ወታደራዊ መሪ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ይሁን እንጂ የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒያ ግድያን ተከትሎ የቡድኑ አጠቃላይ መሪ ሆኖ ተሹሟል።
ይህ ግለሰብ የሐማስ መሪ ተደርጎ ይሾም እንጂ አድራሻውን ካጠፋ ወራቶች አልፈዋል።
ለነገሩ በሺዎች የሚቆጠሩት የእስራኤል ወታደሮች በሰላዮች እና ድሮኖች ታግዘው ያለበትን ለማወቅ በሚያነፈንፉበት ወቅት አድራሻውን ማጥፋቱ አይገርምም።
በነጭ ፀጉሩ እና ችምችም ባለው ጥቁር እና ነጭ ቅንድቡ የሚለየው ሲነዋር፣ በእስራኤል ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሰው ነው።
እስራኤል ለመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ቁጥር አንድ ተጠያቂው ሲንዋር ነው ትላለች።
ሐማስ ቅዳሜ ንጋት ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ከ1200 በላይ እስራኤላውያንን ገድሎ ከ200 በላይ ሰዎችን አግቶ ወስዷል።
ከዚህ ጥቃት ማግስት የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች ቃል አቀባይ “ያህያ ሲንዋር የዘመቻቸው ጠንሳሽ እና መሪ ነው . . . ሞት የማይቀርለት ሰው ነው” ሲሉ አውጀው ነበር።
ከሲንዋር እኩል እስራኤል ሞቱን የምትሻው ሌላኛው የሐማስ ቁልፍ ሰው ሞሐመድ ዴይፍ ነበር።
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ኢዘዲን አል-ቃሲም ብርጌድ መሪ ነው ሞሐመድ ዴይፍ መግደሏን አስታውቃለች።
እስራኤል የሐማስ መሪ ተደርጎ የተሾመው ሲንዋር፣ በጋዛ እንዳለም የእስራኤል ጽኑ እምነት ነው።
የእስራኤል ደኅንነት መረጃዎችን እንደሚያመለክቱት ሲንዋር በጋዛ ልክ እንደ የሸረሪት ድር በተዘረጉት ከመሬት በታቸ ባሉ ዋሻዎች በአንዱ ከግል ጠባቂዎቹ ጋር ተደብቆ፤ የስልክ መስመሬ ሊጠለፍ ይችላል በሚል ስጋት ከተቀረው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳያደርግ ተደብቆ ይገኛል።
በእስራኤል የመከላከያ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ በርካቶች በእስረኛ ልውውጥ ወቅት ሲንዋርን መልቀቅ ትልቅ ስህተት ነው ብለው ያምናሉ።
እአአ 2015 ላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሲንዋርን “ዓለም አቀፍ አሸባሪ” ሲል ፈርጆታል።
ግንቦት ወር 2021 ላይ የእስራኤል አየር ኃይል መኖሪያ ቤቱን እና መሥሪያ ቤቱን ደብድቦ ነበር። ሲንዋር ግን በቦታው አልነበረም።
ሲንዋር 2022 ላይ አደባባይ ወጥቶ ለፍልስጤማውያን በተቻላችሁ መንገድ ሁሉ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሙ ሲል መልዕክት አስተላለፈ።
ተንታኞች በሐማስ ፖለቲካዊ እና በወታደራዊው ክንፍ አልቃስም ብርጌድ መካከል ቁልፉ ሁነኛው ሰው ሲንዋር ነው ይላሉ።
ይህም ብቻ አይደለም የሱኒ አረብ ድርጅት የሆነው ሐማስ፤ የሺዓ አገር ከሆነችው ኢራን ጋር ግንኙነት እንዲያደረጅ ያደረገ ቁልፉ ሰው ሲንዋር ነው ይባላል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሃሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም
