የአሜሪካ አየር መንገድ በቀጣናው እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ እስከመጪው አመት ሚያዚያ ድረስ ምንም አይነት በረራ ወደ እስራኤል እንደማይኖረው ነው የገለፀው።
ከአሜሪካ በተጨማሪ በትንሹ 20 አየር መንገዶች ከእስራኤልም ሆነ ወደ እስራኤል የሚደረጉ በረራዎችን ማቆማቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይህ እርምጃ በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከ40ሺህ በላይ ሰዎች ከተገደሉ እና ከ92ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከቆሰሉ በኋላ በቀጣናው እየበረታ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ የተወሰደ ነው።
አየርመንገዱ እስከ ሚያዝያ 2025 ወደ እስራኤል በረራ እንደማያደርግ ይግለፅ እንጂ ተጨማሪ ጉዳዮችን ግን አላብራራም።
እስራኤል ባለፈው ወር በኢራን መዲና የሀማስን የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሀኒዬህን ከገደለች በኋላ ከኢራን ጥቃት ይደርሳል በሚል በከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጁነት ላይ ትገኛለች።
ኢራን እና ሀማስ ግድያውን እስራኤል ፈፅማዋለች በሚል ክስ ቢያቀርቡም ፤ እስራኤል በበኩሏ ለግድያው ሀላፊነት ከመውሰድም ሆነ ክሱን ከማስተባበል ተቆጥባለች።
በእስከዳር ግርማ
ነሐሴ 09 ቀን 2016 ዓ.ም
