በደሴ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጀሜ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተከሰተው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸው እና ስጋት ውስጥ ያሉ 264 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ ሲል የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ግርማ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ከመኖሪያ ቤታቸው እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎች ቁጥር አሁን ካለበት ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል ።
በደረሰው የመሬት መንሸራተት አንድ የአስፓልት መንገድ መጎዳቱን ተከትሎ በአካበቢ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመጠቀም መቸገራቸውን ተናግረዋል ።
ከቀጣይ ወር ጀምሮም ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ እንደመሆኑ የመንገዱ መዘጋት ህፃናቶች ወደ ትምህርት ለመሄድ ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጥርባቸዋል ብለዋል።
ክረምቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ለማስተካከልም አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
የማህበረሰቡ ነዋሪዎች በእግራቸው አቋራጭ መንገዶችን እየተጠቀሙ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኝ ነግረውናል ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የጉዳቱ መጠን ከፍ እያለ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ማገዝ የሚችል የማህበረሰብ ክፍል በሙሉ እገዛ ቢያደርግ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሐመረ ፍሬው
ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም
