ህወሓት ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ ሾመ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ ተነስተው በምትካቸው አማኑኤል ኣሰፋ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርነት ሁነው ተሹመዋል

በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ ባለፉት ሰባት ቀናት ጉባኤውን ያካሄደው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) በድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡን አስታወቀ።

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ተነስተው በምትካቸው አቶ አማኑኤል ኣሰፋ በምክትል ሊቀመንበርነት መመረጣቸውም ተገልጿል።

በጉባኤው የተመረጡትን 45 አባላት ፓርቲው በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ በዝርዝር ያስታወቀ ሲሆን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በተጨማሪ ዘጠኝ የስራ አስፈጻሚዎችንም ይፋ አድርጓል።

ፈትለወርቅ ገብረእግዚኣቢሄር፣ ልያ ካሳ፣ ተኽላይ ገብረመድህን፣ ዶ/ር ፍስሃ ሃፍተፅዮን፣ ዶ/ር ኣብርሃም ተኸስተ፣ ረዳኢ በርሀ፣ ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳነ ስራ አስፈጻሚ ሁነው መመረጣቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከስድስት አመታት በፊት ስራ አስፈጻሚ በመሆን እንዲያገለግሉ ተሹመው ከነበሩት መካከል አዲስአለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ ጌታቸው አሰፋን እንዲሁም በጉባኤው እንደማይሳተፉ ያስታወቁት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ስድስት አመራሮቹ ከስራ አስፈጻሚነት መነሳታቸውን የፓርቲው መረጃ ያሳያል።

አዲስአለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ ጌታቸው አሰፋ ከስራ አስፈጻሚነት ተነስተው በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደቀጠሉ መረጃው አመላክቷል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *