ተስፋ መቁረጥ!

ተስፋ መቁረጥ ህይወትን ከማጣት የሚተናነስ አይሆንም ይላሉ የስነ-ልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ልዑል አብረሃም፡፡

አቶ ልዑል አብራሃም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ጣቢያችን ከተስፋ መቁረጥ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን ጠይቋል፡፡

አቶ ልዑል ተስፋ ለሰዉ ልጅ የተሰጠዉ ትልቁ ስጦታዉ ነዉ ያሉ ሲሆን ይህም ሰዎች ነገን እዲናፍቁ የሚያደርግ ነዉ ብለዋል፡፡

ተስፋን በምሳሌ ሲያስደግፉት የስነልቦና ባለሙያዉ ፤- ለመኪና መንቀሳቀስ ጎማ እደሚያስፈልግ ሁሉ ተስፋም ለሰዉልጅ እንዲሁ ነዉ ይላሉ፡፡ተስፋ ከሌለ ጨለምተኝነት ይበዛልም ብለዋል፡፡

ሰዎች ተስፋ ለምን ይቆርጣሉ

የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሰዉ ልጆች በተለይ በሕይወታቸዉ አስቸጋሪ ዉጣ ወረድ ዉስጥ ሲገቡ ወይም የማያልፉት የሚመስል ፈተና ሲገጥማቸዉ በዉስጣቸዉ የሚፈጠር ከፍርሀት ፣ከስጋት እና ከእምነት ማጣት የሚፈጠር እጅግ ከባድ ስሜት ነዉ ብለዋል፡፡

-ከዚህ ባለፈ ሰዎች ተስፋን በሶስት መንገድ ሊያጡ ይችላሉ፤-በሰዎች፤በሃሳቦች ፤በነገሮች ብለዋል፡፡

-ተስፋ ብዙም ባይሆን ከድብርት እና ጫና ጋር የሚገናኝበት ባህርይም አለዉ፡፡

-አንዳንድ ጊዜም ይህ ነዉ የሚባል ምክንያት ሳይኖረን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፡፡

-በአንድ ነገር ሰዎች ያረኩ ከሆነና ከሚጠበቅባቸዉ ነጥብ በታች የሚያመጡ ከሆነ የዚህ ስሜት ተጠቂ የመሆን ዕድል ሊኖራቸዉ ይችላል ሲሉም ያክላሉ፡፡

ታዲያ ይህ የስሜት ቀዉስ ወይንም ተስፋ መቁረጥ ከባድ በመሆኑ ከዚህ ስሜት ለመዉጣት ከፍተኛ ትግልና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ነዉ ብለዋል፡፡

ተስፋ ማጣት መገለጫዎች

የኃዘን ወይም የድብርት ስሜት ፤የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የእንቅልፍ እጦት፤ የራስን ጸዳት እና የጤንነት ሁኔታ ችላ ማለት ከቤተሰብ፣ከጓደኞችና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ መራቅ፣በትምህርት፣ በሥራ እና በልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ አለመሆን፡፡

ከፍተኛ የጥፋተኝነትና የሃፍረት ስሜት መሰማት (ሕይወቴ ትርጉም የላትም፣ ለሌሎችም ሰዎች ሸክም ነኝ፣ በሥራዬም ውድቀት እንጂ አሸናፊነት አልቀዳጅም ብሎ ማሰብ)የተስፋ እጦት ከሚፈጠራቸዉ ስሜቶች መካከል የተወሰኑት ናቸዉ ብለዉናል፡፡

ታዲያ የእነኚ ስሜቶች ድምር ራስን ወደ መጉዳት እና ከፍ ሲልም እራስን ለማጥፋት የተለያዩ መንገዶችን ወደ መፈለግ ይመራል፡፡

ከተስፋ መቁረጥ እንዴት እራስን መጠበቅ ይቻላል ?

ተስፋ ማጣት የአንድ እና ሁለት ሰዉ ብቻ ችግር አደለም በቅድሚያ ይላሉ አቶ ልዑል፡፡

ይሄን ካልን ዘንዳ ደሞ ይላሉ የስነልቦናዉ ባለሙያዉ፤-

  • ችግርን በአግባቡ መረዳት

-ከትናንት ምልካሙን እየወሰዱ ክፉዉን አርቆ መጣል እነዲሁም አዲሲ ነገር ለማወቅ ፤ለመስራት እራስን ለለዉጥ ዝግጁ ማድረግ ተገቢ ነዉ ብለዋል፡፡

-ተስፋ መቁረጥ ከተደጋጋሚና አሰልቺ ሕይወት የሚመነጭ ሊሆን ስለሚችል ሥራቹሁን፣ አካባያቹሁን ወይም ለነገሮች ያላቹሁን ዕይታ መለወጥ ከቻላችሁ የችግሩ ተጋላጭ አትሆኑም ሲሉም ያትታሉ፡፡

-ይህ ማንኛዉም የሰዉ ልጅ የሚሰማዉ ነዉ ብሎ ማሰብ እና በእኛ ላይ ብቻ እንዳልተፈጠረ ማሰብ፡፡

በተጨማሪም ሁሉም አዲሲ ቀን የራሱ በረከት እናዳለዉ በማሰብ ትናንት የወደቃቹ ከሆነ ነገ እንደምትነሱ በማመን፣ትናንት ከከሰራቹ ነገ እንደምታተርፉ በማሰብ፣ትናንት ያጣቹትን ነገ እንደምታገኙት በማሰብ በአሉታዊ ሳይሆን በአዉንታዊ በማየት ነገን የተሸለ ማድረግ ይቻላል ብለዉናል፡፡

በመጨረሻም እርዳታ መጠየቅ የበታችነት ባለመሆኑ ፤አንዱን የከበደዉ ቀንበር ላንዱ በመቅለሉ በዚህ የስሜት ቀዉስ ዉስጥ ያሉ ሰዎች ስነልቦና ባለሙያዎችን፤እንዲሁም አጠገባቸዉ ያሉ ከነሱ በላይ ሰዎችን ማማከር ዕርዳታን መጠየቅ ይገባል ሲሉ ምክራቸዉን ለግሰዋል፡፡

በልዑል ወልዴ

ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *