የአሳ ምርትን ወደ ዉጪ ሀገራት ለመላክ የሚያስችል ወጥ አሰራር ባለመኖሩ ከሀገር ዉስጥ መጠኑ ከፍ ያለ የአሳ ምርት በህገወጥ መንገድ እንደሚወጣ ሰምተናል።
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት፤ የአሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ፋሲል ዳዊት በአብዛኛዉ በጋምቤላ እና አማራ ክልል መተማ በኩል በማድረግ ወደ ሱዳን ፤ደብብ ሱዳን እና መሰል የጎረቤት ሀገራት ምርቱ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ህጋዊ እዉቅና እና ፍቃድ ሳይኖራቸዉ ለዉጪ ገበያ የሚቀርብ ትኩስ አሳ እና በቋንጣ መልክ ተዘጋጅቶ፤ በድንበር አካባቢ በስፋት ከተለያዩ ምርቶች ጋር እንደሚጓዝ ሀላፊዉ ገልፀዋል።
ሀገሪቱ በአመት 530 ሺህ ቶን አሳ ማምረት የምትችል ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት አመት 132 ሺህ ቶን ምርት ብቻ መገኘቱን ያነሱት ዶ/ር ፋሲል የአሳ ምርት በተፈለገዉ መጠን ባለመገኘቱ ምክንያት፤ ዘርፉ አለማደጉን አንስተዋል።
ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉ የዉሃ አካላት በተደጋጋሚ የማስገር ጫና ስጋት ላይ ናቸዉ የተባለም ሲሆን ሆኖም ስጋት ዉስጥም ሆነዉ ከምርት አንፃር በተለይ ከሀይቆች የተሻለ ምርት እየሰጡ ነዉ፤ የተባለ ሲሆን፤ ከእነዚህ ጫሞ እና ቱርካና ተጠቃሽ ናቸዉ ብለዋል።
ለዘርፉ ማነቆ የሆኑትን የዘመናዊ ማስገሪያ እና የአሳ ምርት ግብአት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የገለፁት ሀላፊው በአሳ ሀብት ልማት ላይ የባለሀብቶች ተሳትፎ እምብዛም ነዉ ሲሉ ነግረዉናል።
ቁምነገር አየለ
ነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም
