የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮሽች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት መጪው ዘመን መለወጫ በዓል ገበያው ላይ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር ከክሎች ባለፈም ከታንዛኒያ ሽንኩርት ማስገባታቸውን ነግረውናል፡፡
በተለይ የእሁድ ገበያ ላይ ከሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በተያያዘ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን እና ታንዛኒያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ሽንኩርት ወደ ከተማዋ ማስገባት መቻላቸውን አንስተዋል።
በቅርቡ ለተፈጠረው የሽንኩርት መወደድ ምክያትም በሽንኩርት ማሳዎች ውስጥ ውሃ ተኝቶበት እንደሆነ ተናግረው ከኦሮሚያ ከሶማሌ እንዲሁም ከሌሎች ክልሎችም ጭምር ምርት መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ሽንኩርትን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እና ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በጋራ ስራዎችን መሰራቱንም ገልጧል፡፡
ዳይሬክተሩ አላስፈላጊ የገበያ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የመከታተል ስራዎች መሰራታቸውን እና በተለይ ደግሞ ንግድ ፍቃድ ኖሯቸው እየሰሩ ባሉ አካላት ላይ ከፈቃድ ማስጠንቀቂያ እስከ ፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ድረስ እየተሰጠ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በዚህም ለበዓሉ የሽንኩርት፣ የእንቁላል፣ የዘይት፣ የዱቄት፣ የቁም እንሰሳት ፣ የቅቤ፣ የጤፍ ምርቶች ላይ ከኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ከአዲስ አበባ የንግድ ስራዎች ድርጅትና ከህብረት ስራ ኮምሽን ጋር በመቀናጀት ተመጣጣን በሆነ ዋጋ እየቀረቡ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በለዓለም አሰፋ
ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም
