አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ወገቤን አሞኛል ስለዚህ ቆይቼ መታከም አለብኝ በሚል ክለቡን ፍቃድ ጠይቋ እዚያው አሜሪካ ቀርቷል።
ክለቡም የጉዟ ትኬቱን እስከ አርብ በማራዘም ፍቃድ መስጠቱን ሰምተናል።
አሰልጣኝ ነፃነት ወገቤን ልታከም በሚል ፍቃድ ቢጠይቅም እንደሚመለስ ቢናገርም ቅርበት ያላቸው ወገኖች ግን በጭራሽ አይመለስም እያሉ ነው። እርግጥ ነው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ቡድኑ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባነሳበት ወቅት ተጨዋቾቹ ተሸክመውት በሚጨፍሩበት ወቅት የወገብ ህመሙ አገርሽቶበት አሁን ድረስ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ነው።
ስለዚህ የቀረው ሊታከም ነው ቢባል እንኳን ለፍቃድ የጠየቀው ጊዜ በቂ ባለመሆኑ የቀረው ለመታከም ሳይሆን ለመቅረት ነው ሲሉ የቅርብ ሰዎቹ ይናገራሉ።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ቡና ቡድን ዋና አሰልጣኝ
ተደርጎ የተሿመው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ተገቢው መብትና ክብር በክለቡ አልተሰጠኝም በሚል ቅሬታና ተቃውሞ በአመራሩ ላይ እንዳለውም ተነግሯል።
አሰልጣኙ በተጨዋችና አሰልጣኝ ምልመላ፣ በጥቅማጥቅም፣ እንዲሁም በስራ ነፃነትና በመሳሰሉት በክለቡ ደስተኛ ባለመሆኑ ምክንያት በህክምና ሰበብ ሊቀር እንደወሰነና እንደማይመለስ ትናንት ወደ አሜሪካ ያደረግናቸው የስልክ ግንኙነቶች ያስረዳሉ። ይሄን ተከትሎም ክለቡ በቅርቡ የአሰልጣኝ ሹመት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል።
ከሀገር ውስጥ በእጩነት የተያዘው ደግሞ ከያዝነው አመት አጋማሽ አንስቶ ክለቡን በተጨዋች መልማይነት ሲያገለግል የቆየው የቀድሞ የክለቡ ተጨዋችና አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ነው። ጥላሁን ከአሁን ቀደም ክለቡን በተለያዩ ጊዜያት በማሰልጠን ያገለገለ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተጨዋች መልማይነት እያገለገለ ይገኛል።
በክረምቱ ዝውውር ለቡድኑ ከፈረሙት የተወሰኑት በእሱ የተመለመሉም ናቸው።
በጋዲሳ መገርሳ
ጳጉሜ 05 ቀን 2016 ዓ.ም
