የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልዕክታቸው ዘመን ዕድል ነው፡፡ ዘመንን መጠቀም ግን የሥራ ውጤት ነው፡፡ ዘመንን ፈጣሪ ለሁላችንም በእኩልነት ሰጥቶናል፡፡
ልዩነት የሚፈጠረው በዘመን በመሥራትና ባለመሥራት ነው በታሪካችን ውስጥ የምንኮራባቸው ምእራፎች አሉ፡፡ በሕይወታችን ውስጥም ደስ የሚያሰኙን ጊዜያት አሉ፡፡ እነዚያ ምእራፎችና ጊዜያት ሌላ ነገር አይደሉም የተሰጠንን የዘመን ዕድል በሚገባ ተጠቅመን የሠራንባቸው ወቅቶች ናቸው ብለዋል፡፡
እኛ ብንፈልግም ባንፈልግም ዘመን ይለወጣል፡፡ ጊዜ ወደፊት ብቻ የሚሄድ ማሽን ነውና፡፡ ማንም አያስቆመውም፤ አቅጣጫም አያስቀይረውም፡፡ የሚቻለው በጊዜ መጠቀም ብቻ ነው፡፡
“ክረምት ለሰነፍ ገበሬ መዓት፤ ለጎበዝ ገበሬ ምሕረት ነው” ይባላል ምሕረትና መዓቱ ከዝናቡ የሚመጣ ሳይሆን ከገበሬዎቹ ዝግጅትና ሥራ የሚገኝ ነው በሰነፍ ገበሬ ላይ ዘመን ይለወጥበታል፤ ብርቱው ገበሬ ግን ዘመንን ራሱን ይለውጠዋል፡፡
በ2016 ለኢትዮጵያ ምን አሳክተናል? በ2017ስ ለኢትዮጵያ ምን ተዘጋጅተናል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የዘመን መለወጥን ትርጉም ይቀይረዋል ነው ያሉት፡፡
2017 የሚለውጠን ሳይሆን የምንለውጠው ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ፡፡ ዕቅዶቻችንን ተግብረን፤ ፕሮጀክቶቻችንን በጊዜና በጥራት አጠናቅቀን፤ ግጭቶቻችንን በውይይትና በድርድር ፈትተን፤ የዘመናት ስብራቶቻችንን በምክክርና በሽግግር ፍትሕ ጠግነን፤ በብዙ ነገሮች ራሳችንን ችለን፤ ሪፎርሞቻችንን በብቃት አሳክተን፣ የምንለውጠው ዘመን እንዲሆን ነው ምኞቴ ብለዋል፡፡
2017ን በኢትዮጵያ ታሪክ የሚጠቀስ ዘመን ለማድረግ እንዘጋጅ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የዘመናት ዕዳዎቻችን የምናወራርድበት፤ የኖሩ ቁስሎቻችን የምናክምበት፤ የዘመናት ሕልሞቻችንን ሥር መሠረት የምናስይዝበት፤ የታሪክን መኪና መሪና ማርሽ የምንቆጣጠርበት ዘመን ለማድረግ እንነሣ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጳጉሜ 05 ቀን 2016 ዓ.ም
