በቁጥር 22 የሚደርሱ የምራቅ እጢ ካንሰር አይነቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡
በዚ ህመም ከሴቶች በበለጠ ወንዶች እንደሚጠቁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በአለም ላይ በዓመት ከ100,000 ሕዝብ ውስጥ 0.4 እስከ 2.6 የሚደርሱ ሰዎች በዚ ህመም ይጠቃሉ፡፡
የአለም አቀፍ የካንሰር ምርምር ኤጀንሲ በ2020 ባጠናው ጥናትም 53, 583 ሰዎች በዚህ በሽታ መያዛቸውን እና 22 ,778 ሰዎች በበሽታው መሞታቸውን መረጃው ያሳያል፡፡
በጉዳዩ ላይም ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት ከአንገት በላይ ህክምና ስፔሻሊስት እና የመስማት ችግሮች ህክምና ልዩ ስፔሻሊስት የሆኑትን ዶ/ር ሚካኤል ከበደ ናቸው፡፡
የምራቅ እጢ ካንሰር ምንድን ነው ?
ምራቅን የማመንጨት ስራ ያላቸው የምራቅ እጢዎች በአንድ አንድ ምክንያቶች ካንሰር ሲነሳባቸው የምራቅ እጢ ካንሰር እንደሚባል ያነሳሉ፡፡
ይህ አይነቱ የካንሰር አይነት ብዙም ያንተለመደ ነው ይላሉ፡፡
ብዙ አይነት ምራቅ እጢ ካንሰሮች እንደሚከሰቱም ይናገራሉ፡፡
መንስኤው ምንድን ነው?
- የእድሜ መግፋት
- ለጨረር ህክምና መጋለጥ
- በስራችን ምክንያት ለተለያዩ ኬሚካሎች መጋለጥ
- በቤተሰብ ውስጥ የምራቅ እጢ ካንሰር ካለ ሊከሰት ይችላል፡፡
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
- አፋችን አካባቢ ወይም አንገታችን አካባቢ ህመም የሌለው እብጠት
- እየባሰ ሲሄድ ህመም መኖር
- ለመዋጥ መቸገር
- ግማሽ ፊት አልንቀሳቀስ ማለት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ህክምናዎቹ ምንድን ናቸው?
- እጢውን ሙሉ ለሙሉ በቀዶ ጥገና ማስወገድ
- የጨረር ህክምና
- ኪሞቴራፒ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም በአፋችን እና አንገታችን ዙሪያ ያልተለመደ እብጠት የምናስተውል ከሆነ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ እና የሽታው ደረጃ ከፍ ሳይል በጊዜ የሚገኝ ከሆነ ሙሉ ለሙሉ የመዳን እድሉ ከፈተኛ መሆኑን ዶ/ር ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
በሐመረ ፍሬው
መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም
