ሀገራችን ኢትዮጵያን በአለምአቀፍ መድረኮች ላይ የሚወከሉ የቴኒስ ስፖርት ተጫዋቾችን ለማፍራት ለስፖርቱ ልዩ ፍቅር እና ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎችን በዘርፉ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት በዘርፉ በስፋት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ተቋማት መካከል ታሪኩ እና ደስታ ቴኒስ ክለብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ተቋሙ ቴኒስን በመጠቀም ታዳጊዎች በሁለንተናዊ ስብዕና ታንፀው እንዲያድጉ እየሰራ ያለ ተቋም ነዉ።
በተቋሙ በቴኒስ ስፖርት የስልጠና ማዕቀፍ ውስጥ በተለይም ገቢያቸዉ አነስተኛ የሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች እንዲታቀፉ በማድረግ በስፖርቱ፣ በትምህርት እና በአጠቃላይ ህይወታቸዉ ውጤታማ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ተችሏል።
ከሁለት አስርት አመታት በላይ ባስቆጠረዉ የስራ ጊዜዉ ታሪኩ እና ደስታ ቴኒስ ከለብ በተለያዩ የአለማችን ከፍል በስፖርት እና በስኮላርሺፕ ስኬትን ያስመዘገቡ ወጣቶችን ማፍራት ችሏል። በአሁኑ ሰዓትም በክለቡ ውስጥ 80 ያህል ታዳጊዎች ይገኛሉ።
ለእነዚህ እና በአጠቃላይ በሀገራችን ላሉ ታዳጊ የቲኒስ ስፖርተኞች የውድድር እድል ለመፍጠር እና የተሻለ ልምድ ለማስገኘት የሚያስችል ለሁሉም ከፍት የሆነ የቴኒስ ውድድር (TDKET Junior Open 2024) ለማካሄድ ዝግጅቱን ጨርሷል።
ውድድር በሶስት ምድብ ይደረጋል ከ10, ከ12 ኢና ከ14 አመት በታች
የውድድሩ አላማ
➢ ነገ ሀገራችን ኢትዮጵያን በታላላቅ መድረኮች የሚወከሉ ታዳጊ የቴኒስ ተጫዎቾችን ለማፍራት፤
➢ ለቴኒስ ስፖርት ልዩ ፍቅር እና ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማበረታታት፤
➢ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማድረግ፤
➢ በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ታዳጊዎችን ለማሳተፍ፤
➢ የቴኒስ ውድድር ስፖርታዊ ጨዋነትን ለታዳጊዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ለማስተማር ወዘተ.
ውድድሩ
❖ ዛሬ ጥቅምት 15 – የውድድር የመከፈቻ መርሀግብር እና የመከፈቻ ጨዋታዎች
❖ ነገ ጥቅምት 16 – በሁለቱም ፆታ ውድድሮች ይካሄዳሉ
❖ እሑድ ጥቅምት 17 – የፍፃሜ እና የሽልማት እንዲሁም የመዝጊያ መርሀግብር
ጋዲሳ መገርሳ
ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም
