የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በአገራችን ለ19ኛ ጊዜ “የሴቷ ጥቃት የኔም ነው ዝም አልልም” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ህዳር 16 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚከበር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ሂክማ ሄይረዲን፤ የቀኑ አከባበር አጠቃላይ ዓላማ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አስከፊነት ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ፆታዊ ጥቃት እንዲቀንስ እና እንዲወገድ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ጥቃት የደረሰባቸውንም ዜጎች ለመደገፍ ታስቦ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በቀጣይ ለ16 ተከታታይ ቀናትም በሁሉም ዩንቨርስቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣ በሀይማኖት ተቋማት፣ በመስሪያ ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ጥቃትን እንዲከላከሉና እንዲያወግዙ የንቅናቄ ዘመቻ የማድረግ እና ሀብት የማሰባሰብና ድጋፍ የማድረግ ስራዎች እንደሚሰሩም አንስተዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፤ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአገልግሎት ሥርዓትን በመዘርጋት ተግባራዊ በማድረግ በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ ማህበራዊና ሥነ – ልቦናዊ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው፤ ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ሚኒስትር ድኤታዋ ሁላችንም ጥቃትን ለመከላከል እና ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ኀዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
