የምርመራው ትኩረት በባጃጅ ያዘዋወሩ ፣የድላላ ስራ የሰሩ እና ጥቂት ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ላይ ነው ተብሏል።
መንግስት ከፍ ወዳለ የምርመራ መንገድ መግባት አለበት ያሉት በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ ትብብር ጥምረት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ናቸው።
ሃላፊው፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እጅግ በጣም ውስብስብ የሆነ ነገርግን በሚፈለገው ልክ በመንግስትም ትኩረት ያላገኘ ችግር ነው ብለዋል።
በየጊዜው በመጥፎ ሁኔታ ወደ አገራቸው የሚመለሱ፣ ህይወታቸው የሚያልፍ ዜጎቻችንን ለመታደግ ከፍተኞቹ የሰዎች ነጋዴዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት ነው ያሉት።
መንግስት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ኔትዎርኩ ላይ ትኩረት አድርጎ ምርመራ እና ክርክር እንዲያደርግ ሚዲያዎችም የበኩላቸውን ሊያደርጉ እንደሚገባም አንስተዋል።
የችግሩን መሰረታዊ ምክንያት ማወቅ እና መለየትም ሌላው መፍትሄ እንደሆነ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የአገራችን ዜጎች የኢኮኖሚ ፍልሰተኞች ናቸው የሚሉት አቶ አብርሃም ፤ በአገር ውስጥ መደረግ የሚችሉ ጉዳዮች መፍትሄ ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
ወንጀሎቹ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆናቸው ከሌሎች አገራት ጋርም እየተሰራ ነው ያሉት ሃላፊው፤ በአገር ውስጥ ግን መንግስት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።
እስከዳር ግርማ
ታኀሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም
