መነሻ ምክንያቶች ምንድናቸዉ?
የጉንፋን ሕመም በተፈጥሮ የላይኛውን የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎች ማለትም አፍንጫን፣ ጎሮሮን እና የአየር መተላለፊያ ባንቧን የሚያጠቃ ተላላፊ ሕመም ነዉ።
‹‹ሪኖ ቫይረስ›› ለጉንፋን መከሰት ዋና ምክንያት ሲሆን፣ ኮሮና፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራ ኢንፍሉዌንዛ፣ አር ኤስ ቪ(RSV) ቫይረሶች ደግሞ
ለጉንፋን መሰል ህመሞች መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸዉ።
ከተጠቀሱት ቫይረሶችም ለጉንፋን ሕመም መከሰት 50 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ‹‹ሪኖ ቫይረስ››ነው፡፡
በደረቅ ነፋሳማ ወቅት የአፍንጫ የውስጠኛው ስስ ሽፋን “ሙከስ መምብሬን” ስለሚደርቅ የጉንፋን ሕመም እና ተላላፊነቱ ይጨምራል፡፡
የክረምት ወራት ወይም የዝናብ ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ መስከረምን ጨምሮ በጥቅምትና ህዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ህመም የሚጠበቅ ነው፡፡
መተላለፊያ መንገዶች
ሕመሙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ ነዉ፡፡
በተጨማሪም ሰዎች ቫይረሱ ያረፈበትን የበር እጀታ፣ ጠረጴዛ ወይም በሕመምተኛው የተነካን ሰው እጅ ከነኩ በኋላ አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሲነካኩ ቫይረሱ ለመተላለፍ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል ማለት ነዉ፡፡
ምልክቶቹ
ህመሙ አብዛኛዉን ጊዜ እስከ 2 ሳምንት ሊቆይ ይችላል።
የጉንፋን ሕመም የመጀመሪያ ምልክቱ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት ተላላፊ ሊሆን ይችላል፤ ሕመሙ ከጀመረ ከ 5 እስከ 10 ባሉት ቀናት ደግሞ ሕመምተኛው ቫይረሱን ያስተላልፋል።
ምልክቶቹም እንደ የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታትና ጉሮሮን መከርከር፣ ማስነጠስ፣ አይን ማሳከክ እና መቅላት፣ ማስታወክ፣ ከፍ ሲልም የትንፋሽ ማጠር፣ ከፍተኛ ድካምና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ።
ተጨማሪ ጉዳቶች
አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ በሽታው የመዛመት እድሉ ከፍ ሊል ይችላል፡፡
በተለይ ቀዳሚ ተጎጅ የሚሆኑት ህጻናትና አረጋውያን ናቸው፡፡
እንደ አስም፣ የስኳር በሽታ፣ ካንሰር እና ሌሎች ሥር የሰደዱ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያሉባቸው ሕሙማን ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግላቸው ይገባል፡፡
ወደ ጤና ተቋማት በመሄድም አስፈላጊዉን ምርመራና ህክምና ማድረግም ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም የጉንፋን ሕመም የጆሮ ኢንፌክሽን እና የሳንባ ምች ሕመምን ጨምሮ ለተለያዩ ሕመሞች ተጋላጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡
መከላከያ መንገዶች
ጉንፋን መሰል በሽታን ከምንከላከልባቸው መንገዶች መካከል የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣
ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ የአፍና አፍንጫ ጭምብል(ማስክ) ማድረግ
በዕለት ኑሯችን የምንጠቀምባቸውን በከባቢዎቻችን የሚገኙ ቁሳቁሶችን ማጽዳት
የብዙሃን ማጓጓዣ ትራንስፖርት ላይ መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝዉዉር እንዲኖር በማድረግ የበሽታዉን የመተላለፍ ዕድል መቀነስ ይቻላል፡፡
የበሽታው ምልክት የሚታይበት ሰው በፍጥነት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ምክር እና ዕርዳታ ማግኘት አለበት፡፡
መረጃዉ ከቅዱስ ጳዉሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የተገኘ ነዉ፡፡
ታኀሣሦ 23 ቀን 2017 ዓ.ም
