በያዝነው ሳምንት ሐማስ ስድስት ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን እስራኤል ደግሞ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሰሜናዊው ክፍል ወደሚገኘው ቀያቸው እንዲሄዱ እንደምትፈቅድ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናገሩ።
ከታጋቾቹ መካከል አርቤል የሁድ የተባለች እስራኤላዊት የምትገኝበት ሲሆን እስራኤል አርቤ ካልተለቀቀች ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዳያልፉ ከልክላ ነበር።
ባለፈው ቅዳሜ ሐማስ አራት ወታደሮች ለቋል። ነገር ግን አርቤል እስካሁን አልተለቀቀችም። ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሷል ስትል እስራኤል ወቅሳለች።
በስምምነቱ መሠረት ሲቪል እስራኤላዊያን ታጋቾች ከወታደሮች ቀድመው መፈታት በምትኩ በእስራኤል እስር ቤት የተያዙ ፍልስጤማዊያን መፈታት አለባቸው።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባር ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ ሰባት ታጋቾች እና ከ200 በላይ የተያዙ ፍልስጤማዊያን ተለቀዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩት ፍልስጤማዊያን ወደ ሰሜን ጋዛ መሻገር ፈልገው በእስራኤል ወታደሮች ክልከላ ተጥሎባቸው ቆይተዋል።
እስራኤል እና ሐማስ እስረኞችንና ታጋቾችን ለመልቀቅ እና ተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማሙት በአውሮፓውያኑ ጥር 19 ሲሆን እስካሁን ሁለት ጊዜ ልውውጥ አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እሑድ በሰጡት አስተያየት ግብፅ እና ጆርዳን ፍለስጤማዊያንን ከጋዛ እንዲወስዱ ጠይቀዋል። ፕሬዝደንቱ ጋዛን “የወደመ ሥፍራ” ሲሉ ገልፀውታል።
ሐማስ እና የፍልስጤም አስተዳደር ይህን የትራምፕ ሐሳብ የነቀፉት ሲሆን ግብፅና ጆርዳንም እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ሐማስ በእስራኤል ምድር ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎ ገድሎ 251 ታጋቾች ይዞ መሄዱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም
