የሀይማኖት መሪዎች በርካታ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ቢኖሩም በአግባቡ መጠቀም አልቻልንም ብለዋል።
ይህ የተባለዉ በኢትዮጵያ ሲቪክ እና ሙያ ማህበራት ኮንግረስ አዘጋጅነት በተካሄደው መድረክ ላይ ነዉ።
በኢትዮጵያ አሁን እየተስተዋለ ያለውን ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮች መነሻ በማድረግ በሀይማኖት አባቶች ሀገራዊ የሰላም ጥሪና የጸሎት መርሃ ግብር ተካሄዷል።

በአንድ አንድ የኢትዮጰያ ክፍሎች ያለው አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት እንዲሁም ክፉ የወንጀል ድርጊቶች ለሀገራችን የሚመጥኑ አይደሉም”ያሉት የሀይማኖት አባቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ባለመድረሳችን ሰላም እየደፈረሰ የሀይማኖት ልዕልና እየላላ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት የሰላማዊ ሰዎች መጎዳት፣ የአንድነት መሻከር፣ በድርቅ መመታት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ለጎርፍ እና ለመሬታ ናዳ እየተጋለጥን ለሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች እየተጋለጥን እንገኛለን” ሲሉ ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የጸሎት መርሃ ግብር ያካሄዱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ጨምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የፕሮቴስታንት እምነት አባቶች ተገኝተው በሰላም ጉዳይ የጸሎት መርሃ ግብር አከናውነዋል።
ሰላምን ለማጽናት የሀይማኖት አባቶች የፖለቲከኞች የመሪዎች እንዲሁም የሁሉም ማኅበረሰብ ሚና ከፍተኛ ነዉ ተብሏል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ጥር 30 2017 ዓ.ም
