ከ5 ሺ በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጡ።

ጠጥተዉ ሲያሽከረክሩ የነበሩ ከ5ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ተባለ፡፡

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገነት ዲባባ፤በባለስልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገ የጠጥቶ ማሽከርከር የቁጥጥር ስራ 5 ሺህ 1መቶ73 አሽከርካሪዎች ጠጥተዉ ሲያሽከረክሩ ተገኝተዋል ብለዉናል ፡፡

ወ/ሮ ገነት በቅርቡ በወጣዉ በመንገዶች ትራንስፖርት ትራፊክ ደንብ 557 /2016 መሰረት ጠጥተዉ ሲያሽከረክሩ በነበሩ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በደንቡ ዉስጥ ጠጥቶ ማሽከርከር በልዩ የጥፋት ደረጃ ተቀምጧል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በደንቡ ከተራ ቁጥር ስድስት እስከ ዘጠኝ ያሉት፤ አንድ ሰዉ ጠጥቶ ሲያሽከረክር ምን ያህል መቀጣት አለበት የሚለዉን አሽከርካሪዉ በወሰደዉ የአልኮል መጠን ተቀምጧል ብለዉናል፡፡

በአሽከርካሪዎች ላይ ለሚደረገው የአልኮል መጠጥ ምርመራ የሚያግዝ አዲስ አልኮል ቴስተር አሰራር መሰረት፤ ከ0.24 እስከ 0.6 ሚሊግራም በሊትር ጠጥቶ የተገኘ አሽከርካሪ ሦስት ነጥብ ተጽፎበት 1ሺህ 5 መቶ ብር ይቀጣል ብሏል፡፡

ከ0.6 እሰከ 0.8 ሚሊግራም በሊትር ጠጥቶ ሲገኝም በተመሳሳይ 3 ነጥብ ተሰጥቶት በገንዘብ የ 2 ሺህ ብር እርምጃ ይወሰድበታል ሲሉ ነግረዉናል፡፡

ከ0.8 እስከ 1 ሚሊ ግራም በትንፋሹ የተገኘበት አሽከርካሪ 8 ነጥብ ተመዝግቦበት በገንዘብ የ2 ሺህ ብር እርምጃ የሚወሰድበት ሲሆን፤ ከ1 ሚሊግራም በላይ በትንፋሹ የተገኘበት አሽከርካሪም የ3 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጠብቀው ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ቅጣት ዋነኛዉ አላማ ለማህበረሰቡ ግንዛቤን መፍጠር ነዉ ያሉት ዳይሬክተሯ ፤የቅጠት ደረጃው መንጃፍቃድን ከመንጠቅ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ እንዳያሽከረክሩ እስከ ማገድ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

ልአኡል ወልዴ

የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *