አዋሽ ባንክ በተለያዩ ምክንያቶች አብረውት መስራት ካቆሙ ደንበኞቹ ጋር በድጋሚ ለመስራት ማቀዱን ገለፀ።
ባንኩ የደንበኞችን ሳምንት ሲያከብር በዕቅድ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል በተለያዩ ምክንያት ከባንኩ ጋር መስራት ካቆሙ ደንበኞቹ ጋር በድጋሚ መስራት የሚለው ዋነኛው መሆኑ ተገልጿል ።
ባንኩ ከዛሬ ጀምሮ የደንበኞችን ሳምንት በዋናው መስሪያ ቤትና በሁሉም ቅርንጫፎች በማክበር ላይ ይገኛል።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው፤ ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚከበረው የደንበኞች ሳምንት ደንበኞችን ለማመስገን መታቀዱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያጋጥሙ ክፍተቶች ላይ አስተያየት መስጠት የሚችሉበትን አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ14 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራቱን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ከብር 2መቶ73 ቢሊየን በላይ ተቀማጭ መሰብሰቡንም ገልፀዋል።
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ3መቶ97 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዋሽ ባንክ “ለላቀ የደንበኞች እርካታ እንተጋለን” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደንበኞች ሳምንትን እያከበረ ይገኛል።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም
