የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ጋዛ አፈናቅሎ ወደ ሌሎች አገራት ለማስፈር የያዙት እቅድ “እውን ለማድረግ” እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ።
ቤንያሚን ኔታንያሁ እሁድ ዕለት በኢየሩሳሌም ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ከተገናኙ በኋላ በፍልስጤም ግዛት “የጋራ ስትራቴጂ” ላይ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ውይይቱ የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን እንድትወስድ እና እዚያ የሚገኙትን ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ወደ ጎረቤት አገራት እንድታፈናቅል ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማንኛውንም ዜጋ በቁጥጥር ስር ከሚገኘው ግዛት በግዳጅ ማፈናቀል “ከዘር ማጽዳት ጋር የሚስተካከል” እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የፕሬዚዳንት ትራምፕ እቅድ ሰዎችን “ሊያስደንቅ እና ሊያስደነግጥ ይችላል” ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ “እርባና ቢስ ሀሳቦች” በተሻለ ሌላ አማራጭ ሀሳብ ለማቅረብ “ድፍረት” ይጠይቃል ብለዋል።
ኔታንያሁ እርሳቸው እና ሩቢዮ የትራምፕን የማፈናቀል ራዕይ ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸው አሜሪካ እና እስራኤል በጋዛ ላይ አንድ አቋም አላቸው ብለዋል።
የእስራኤሉ መሪ በትጥቅ ቡድኑ ሃማስ የተያዙ እስራኤላውያን ታጋቾች በሙሉ ካልተለቀቁ “የገሃነም በሮች” እንደሚከፈቱ አስጠንቅቀዋል።
የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም
