ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ
ቢሮው ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት ሊውል የሚገባውን ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ያለባቸውና በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ዕዳቸውን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ 62 ግለሰቦችን በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ ከ1-3 ለተቋሙ በተሰጠ ስልጣን መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን አሳውቋል፡፡
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት የግብር ዕዳቸውን በአግባቡ ሳይወጡ የሚሰወሩ ግብር ከፋዮችን በአግባቡ በመከታተል ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የዕዳ ክትትልና አስተዳደር የስራ ክፍልን በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደ ተግባር ማስገባቱን የገለጸው ቢሮው በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ መሰብሰቡን ገልፆል፡፡
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ቢሮው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም
