ለቡና ዋጋ መጨመር የግብይት ሰንሰለቶች ጤናማ አለመሆን በምክንያትነት ተቀምጧል፡፡
ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በምርት ገበያ የቡና ዋጋ በዕጥፍ መጨመሩን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡
ጣቢያችን በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ ከወራት በፊት አንድ ኪሎ ቡና ከ600 ብር ጀምሮ ይሸጥ የነበረ ሲሆን ከሰሞኑ አንድ ኪሎ ቡና ከ800 እስከ 900 ብር እና ከዛ በላይ እየተሸጠ እንደሚገኝ በቅኝታችን ማረጋገጥ ችለናል፡፡
ወደ ገበያ የሚቀርበው የቡና መሸጫ ዋጋው እንደየ ጥራቱ ቢለያይም ከዝቅተኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የጥራት መጠን ያለው ቡና በአማካይ እስከ 200 ብር የዋጋ ጭማሪ መኖሩምን ከሸማቾች እና ነጋዴዎች ሰምተናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሀሳብ እንዲሰጡበት የጠየቅናቸው በኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳዲ ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተቆላ ቡናን እስከ 800 ብር እንደሚያቀርቡ ነግረውናል።
እስከ 1500 ብር የሚሸጥ ቡና በሃገር ውስጥ እንዳለ በማንሳት ይህም ጭማሪው እንዳለ አመላካች ነው ብለውናል፡፡
ዋና ስራ አሰኪያጁ በገበያው ላይ ምርት እንዲጠፋ የሚያደርጉ የተለያዩ የግብይት ሰንሰለቶች ጤናማ አለመሆን ለመጨመሩ አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
በሀገሪቱ ያለው የቡና ተጠቃሚ ቁጥር ከፍተኛ መሆን፤ በኢትዮጵያ የቡና መሸጫ ዋጋ ለመወደዱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከአፍረካ በአንደኛነት፣ ከዓለም ደግሞ ብራዚል፣ ቬትንሀም፣ ኮሎምብያ እና ኢንዶኔዢያን ተከትላ 5ኛ ደረጃ እንደተቀመጠች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለአለም አሰፋ
መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም
